Friday, 7 September 2018

የግብረ ገብ እጦት በኢትዮጵያ

ባለፈው ጽሁፌ የቻይና የአምባገነናዊ ስረዓት የህዝቡ ግብረ ገብ እጦት ስልጣኑን ለመቀጠል እንደሚመቸው አስረድቼ ነበር (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/08/blog-post_31.html)። ይህን ለማስረዳት በቅርብ ያረፉት የቻይና ፖለቲካ ተንታኝ ሊዩ ሺያኦቦ የጻፉትን ተርጉሜ አብራራሁኝ። እሳቸውም እንዲህ አሉ፡

«ህዝቡ የፖለቲካ ነፃነት ከመጠየቅ በርክሰት እንዲጨማለቅ ያረገዋል።»

በኢትዮጵያም እንዲሁ ነበር። የኢህአዴግ መንግስት በተለይ ላለፉት 13 ዓመት ከምርጫ 1997 በኋላ በ«ልማታዊ አስተዳደር» መፈክር ህዝቡን «ገንዘብ ስሩ አብታም ሁኑ ግን በፖለቲካ፤ ፍትህ፤ ሰላም አትምጡብኝ» ብሎ አዘዘ።

እኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ኤኮኖሚው ሲአድግ ገንዘብ ስናገኝ ፖለቲካ፤ ፍትህ እና ሰላም ምን ያደርጋል ሆዳችን እስከሞላ በገንዘባችን እስከንደላቀቅን አልን (http://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2016/09/blog-post_14.html)። ጎረቤታችን መሬቱ ለ«ልማት» ተብሎ ሲወሰድበት እንኳን ለመንግስት ታቃውሞ ማቅረብ ጎረቤታችንን በትንሽ ገንዘብ አልረዳነውም። ለመንግስት ተቃውሞ ብናሳይ ህልውናችን አሳሳቢ ይሆናል ግን ለጎረቤታችን ትንሽ ብር ብንሰጠው ምንም አንሆን። ግን ይህንንም አላደረግንም።

ገንዘብን ስናሳድድ ጉቦ ብንጠየቅ እንደምንም አድርገን ላለመክፈል ከመሞከር ይልቅ አይናችንን ሳናሽ እንከፋላለን። ከተቻለ ደግሞ ጉቦ ጠያቂም እንሆናለን! ለገንዘብ ወይንም ለንግዳችን ማጭበርበር ካስፈለገን እናጭበረብራለን። ከሰዎች አለአግባብ የተነጠቀ ሃብት ለመጠቀም እድል ካገኘን እንጠቀምበታለን። ሃብት ለማከማቸት ህሊናችን በምንም መንገድ አይከለክለንም።

ይህንን ሁሉ ስናደርግ የግብረ ገብ እጦት ወይንም የክፉ መንፈስ በውስጣችን እያደረ ይሄዳል። በገንዘብ ዙርያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነበር ህሊናችንን እናወድቀዋለን። በማህበራዊ ኑሮ፤ በቤተሰባዊ ኑሮ ወዘተ ወደ ርክሰት እንገባለን። ወደ ዝሙት እንገባለን። በዚህ ምክንያት መጠጥ ቤቶች አለ ቅት ይስፋፋሉ። ሴተኛ አዳሪዎች ይበዛሉ በየ መንገዱ በየ መሸታ ቤቱ በየ ሆቴሉ ይገኛሉ። ልጆቻችንን ለዚህ «ስራ» እናቀርባቸዋለን ገንዘብ እንዲሰሩልን። የልጆች የውሲብ ክስተት ይስፋፋል ዓለም ዙርይ በዚህ እየታወቅን እንሄዳለን። ወዘተ። ህሊናችን ይጣመማል ግብረ ገባችን ይጠፋል።

ለዚህ ሁሉ የሚያበቃን ሁለት ነገሮች አብሮ ሲመጡ ነው። እነዚህ ገንዘብ ውየንም ሃብት እና ሁለተኛው ሀፍረት ነው። ኤኮኖሚው እያደጋ በማጭበርበርም በመስራትም ገንዘብ እናገኛለን። ግን በርካታ ሰዎች ሲጎዱ እናያለን። ቤት እና መሬታቸው ለ«ልማት» ሲነጠቅ፤ ሲታሰሩ፤ በእስር ሲሰቃዩ፤ ከስራ ሲባረሩ፤ በተለያየ መንገድ በመንግስትና ከመንግስት ቅርበት ባላቸው ሲጭቆኑ ወዘተ እናያለን። የሰላም እና የፍትህ እጦትን በደምብ እናያለን። ግን በአንጻሩ ኑሮአችን ተመችቷል። ሃብት እያከማችን ነው። ሰው ማለት ባለ እንጀራዬ ይጎዳል ልረዳው ምንም አላደርግም። ግን እኔ «እየተመቸኝ» ይሄዳል።

ይህ በኛ ቁጭት፤ ጸጸት (guilt) እና ህፍረትን ያመጣል። ህሊናችን ይወጋናል። ሃብታችን ከግብረ ገብ እጦት ጋር አብሮ እንደመጣ እናውቀዋለን። ግን በትክክሉ ተጸጸተን ወደ ንስሐ ለመቀየር ይከብደናል። ይህን ከማድረግ ፋንታ ጸጸታችን እና ህፍረታችን ልባችንን እየቆረጠን እያለ ስለሆነ ወደ ማደንዘዣ እጽ እንሄዳለን። የቅንጦት ኑሮ፤ ዝሙት፤ ስለ ሃብት ብቻ ማሰብ ወዘተ እጽ ናቸው። ጎረቤተ ሲሰቃይ ዝም ብዬው ወደ መጠጥ ቤት የምሄደው ስለ እሱ እንዳላስብ እንዳላየው ነው።

አምባገናናዊ የ«ልማት አስተዳደር» ሰውን እንዲህ ነው የሚያደርገው። የደነዘዘ ገብረ ገብ የሌለው ማህበራዊ ኑሮ የሌለው እርስ በርስ የማይተሳሰብ ህዝብ ነው የሚፈጥረው። የሚፈጥረው ብቻ ሳይሆን የሚፈልገው። ህዝቡ እርስ በርስ ሲራራቅ፤ መተማመን ሳይኖር፤ ማህበራዊ ኑሮ ከሌለ፤ ብጨኝነት ከበዛ ወዘተ ለአምባገናናዊ ስረዓቱ ይጠቅመዋል። ህዝቡ በገንዘብ፤ ቅንጦት እና ዝሙት «እጽ» ሲባክን ስለ ሰላም፤ ፍቅር፤ ፍትህ እና የፖለቲካ ለውጥ አያስብም። አልፎ ተርሮ እራሱ በሚያደርገው ስለሚያፍር መንግስት ሲጨቁን ብዙ አይሰማውም! ዓለም በሙሉ ክፉ ሆኗል ብሎ እራሱን ያሰምናል።

በዚህ መንገዱ ነው አሁን በሃገራችን ላይ ያለው ልክ የለሽ የግብረ ገብ እጦት የመጣው። ለዚህም ነው «ልማት» ወይንም «ልማታዊ አስተዳደር» የሚለው መፈክር ከሀገራችን መጥፋት ያለበት (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_5.html)። የሀገር ህዝብ ማንነት ከሃብት ጋር በዋናነት ከተቆራኘ የግብረ ገብ እጦት መምጣቱ አይቀርም። ይህ ለሰው ልጅ ጤናማ አይደለምና።

አሁን የጠ/ሚ አብይ መንግስት ይሄንን ለመለወጥ እጅግ ከባድ ስራ ነው የሚሆንበት። ከተሳካም የዓመታት ከባድ ስራ ይጠይቃል። የቤተክርስቲያን እና የመስጊድ ታላቅ ስራ ያስፈልገዋል። ግን ዛሬ ባይመስልም አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉት የሀገር ህልውና ጉዳይ ነው እና ጠንክረን ብንሰራበት ነው የሚበጀን።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!