Monday, 10 September 2018

ቤተ ክርስቲያን በፍጥነት መፅዳት አለባት

ቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅ ፓትሪአርክ በሆኑበት ዘመን 11 ፓፓሳትን አባረዋል ይባላል። ቅዱስ ጳውሎስ በመልክቶቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ንፅሁ የሆኑ፤ ጥሩ ምሳሌ የሆኑ እና ህዝቡን የማያሳስቱ መሆን አለባቸው ብሎ በተደጋጋሚ ጽፏል። በርካታ መልክቶቹ ውስጥ ስለቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለን ችግር እና እንዴት መጽዳት እንዳለበት ጽፏል። በዛሬው ዘመን ይህንን የቅዱስ ጳውሎስ ምክሮችን እና የቅዱስ ዮሃንስ አፈወርቅን ምሳሌ ብንከተል ወይንም ቢያንስ ብናስብበት ጥሩ ይመስለኛል።

በቤተ ክርስቲያናችን አመራር ማለትም ጳጳሳት፤ ካህናት እና አስተዳደር በርካታ የእምነት እና ግብረ ገብ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ ችግሮች በተለየዩ መንገዶች ባለፉት ዓመታት መጥተዋል በዝተዋል። ይህ ችግር ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ጉዳት እያመጣ እንደሆነ ይታወቃል።

ስለ የቤተ ክርስቲያን አመራር ችግሮች ስንወያይ ታላቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤

1. ግብዝነትን እና ትዕቢትን መራቅ አለብን፤ እንደ አንድ ምዕመን አመራር ላይ ጣቴን ሳተኩር የራሴን ኃጢአቴን እረሳለሁ። ለዚህ ነው ምዕመናን መሪዎችን እና የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካን አትመልከቱ ብሎ የሚመከረው በክርስትና ህይወት።

2. መፍረድ የለብንም። አመራሮች ላይ ችግር ስናይ ሰው በመሆናችን አንዱን ታላቅ ኃጢአት «መፍረድ» ለማድረግ እንፈተናለን። «ድርጊቱ ላይ እንፍረድ ሰውዉ ላይ ግን መፍረድ የለብንም» የሚለውን ትምሕርት ብናውቅም እንረሰዋለን። መርሳት የልብንም። አመራር ሲሳሳት ብናይ በመጀመርያ ለዛ ሰው መጸለይ ነው ያለብን እና እግዚአብሔርን ሁላችንን ከኃጢአት እንዲያርቀን መለመን ነው ያለብን።

ይህን ካልኩኝ በኋላ ግን ቦትዬ ባይሆንም ለህሊናዬ አደገኛ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ሃሳቤን መነገሬ ጥሩ ይመስለኛል። ቅዱስ ጳውሎስ በመልክቱ እንደዚህ አይነት ጉዳዮች የ«እረኝነት» (pastoral) ጉዳዮች እንደሆኑ ገልጿል። ለምሳሌ ተደጋጋሚ ህዝብ የሚያውቀው ኃጢአቶች የሚፈጽም ካህን ወይንም ጳጳስ ካለ አለቆቻቸው ምን እናድርግ ሲሉ እንደ ዘመናዊ ፍርድ ቤት ህግን ከሞላ ጎደል በጭፍን መልኩ አያሰፍኑም። ምን ቢደረግ ነው ካህኑ የሚድነው? ምን ቢደረግ ነው ህዝቡ የሚድነው? ነገሮች ሚዛን ላይ ተደርገው መታየት አለባቸው እንጂ ጥቁር እና ነጭ አይደሉም። አራት መስፈርቶች፤ ክስተቱ፤ ሁኔታው፤ ሰዎቹ እና ዘመኑ መታየት አለበት።

በኔ እየታ በአሁኑ ዘመን ትሉቁ ጎልቶ የሚታየው መስፈርት «ዘመን» ነው። ምዕመናን በመሪዎች ስህተት በጣም ሊወዛበቡ የሚችሉበት ዘመን ነው። ዛሬ አይኑ ብዙ ነው። ወሬው እና ጫጫታው ብዙ ነው። አንድ ችግር ያለው ጳጳስ ወይንም ካህን ቶሎ ከስራ ካልተወገደ በርካታ ምዕመን በፍጥነት መሰናከል (በእምነት ማጣትም በመፍረድም) የሚችልበት ዘመን ነው። የፍጥነት ዘመን ነው። አንድ ችግር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲገባ በሽታው በፍጥነት ነው የሚስፋፋው እና መሰረት የሚጥለው።

ይህን በሲኖዶስ ችግራችን በደምብ አይተነዋል። አሁን በቤተ ክርስቲያን አመራሮቻችን የጉቦ፤ ሙስና እና ሌሎች የግብረ ገብ እጦት በምዕመናን ያመጣው ችግርን አይተነዋል። ከኛ ቤተ ክርስቲያን ውጭም በካቶሊች ቤተ ክርስቲያን ችልተኝነት እና መታገስ ባለፉት 30-40 ዓመት ያመጡት ችግሮችን አይተናል።

ስለዚህ አሁን እረኞቻችን ሚዛኑን ከትዕግስት ይልቅ ወደ ፍትነት እና ችኮላ ማድላት ያለባቸው ይመስለኛል። እንደ ዮሃንስ አፈወርቅ ጎልቶ የሚታይ ችግር ሲፈጸም ቶሎ ብሎ ህዝቡ ሳይሰናከል እርምጃ መውሰድ። በሽታው መሰረት ለመጣል እና መስፋፋት እድሉ ሳይኖረው ወድያው ማከም። ይህ በዛሬው ዘመን ለኃጢአት አድራጊውም እጅግ ይጠቅመዋል። በፍጥነት ወደ ኃጢአት ኑሮ ውስጥ ከሚገባ ቶሎ ወደ ንስሃ እንዲገባ ይረደዋል። ይህ የፍጥነት ዘመኑ በቀላሉ እንዳይቆጣጠረው ይረደዋል።

ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን አመራሮች እባካችሁን የቤተ ክርስቲያን ጽዳት ዘመቻችንን አፋጥኑ። ችላ አንበል። ታጋሽ አንሁን። በማንም አንፍረድ በስራው ብቻ። ግን ህዝቡን ከፈተና እንጠብቅ። ግልጽና ግዙፍ ኃጢአትን የሚፈጽሙት ጳጳሳት እና ካህናትን ቶሎ ከሃላፊነት ይወገዱ እና ወደ ክርስትናዊ ህክምናቸው ይግቡ። የአሁኑ ዘመን ይህን መንገድ የሚያስገድድ ይመስለኛል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!