Wednesday 4 April 2018

ዜና (ወሬ) ያጃጅላል ባርያ ያደርጋል!

በ2017/11 የተጻፈን ትርጓሜ

አባቴ ኢትዮጵያዊ ምሁር ነበር ማለት ይቻላል። ቤታችን እንደሌሎች የኢትዮጵያዊ ምሁራን ቤቶች የፖለቲካ የፍልስፍና ውይይት ስፍራ ነበር። እኔና አባቴ ብቻችን ሆነንም ከጓደኞች ከእንግዶች ጋርም ምሳ እራት ዝግጅት ሲኖርም «ሁለት ወይም ሶስት» ሆነን በተገኘን ቁጥር ፖለቲካ አብሮን ነበር!

የፖለቲካ ዜናም በቴሌቪዥን እንከታተል ነበር። ከጥቂት ኮሜዲዎች ወይንም የካውቦይ ፊልሞች በቀር ዜና ብቻ ነበር የምንከታተለው። ዋናው ዜና ነበር። ወደ ሰሜን አሜሪካ ስንፈልስ ደግሞ ዜና እስከሚበቃን ማየት ቻልን! የፖለቲካ ትንታኔ ፕሮግራሞችም በሽ ነበሩ።

ዜናን በመከታተላችን እራሳችንን የተማርን ሊቆች ብለን እንቆጥር ነበር። እንደሌሎች ሰዎች የማይረቡ ትርዒቶች አናይ! የሰለጠንን ምሁራን ቁም ነገረኞች ነበርን! ጎረቤቶቻችን ሜክሲኮም እንኳን የት እንደሆነ የማያውቁ ሲሆን እኛ አብዛኞቹ የዓለም ዋና ከተሞችን እናውቃለን። የአሜሪካ የፕሬዚደንት ምርጫ ክርክሮችንም እንከታተላለን። ያውም ምርጫው ገና በእጪ ደረጃም ሆኖ! ስልጣኔአችን የተለየ ነበር!

ግን እውነቱን ለመናገር ይህ ሁሉ ትርጉምም ቁም ነገርም አልነበረውም። የኛ የዜና መከታተል ከቤት እመቤት የድራማ ትርዒት መከታተል ከወጣቱ የስፖርት ግጥምያ መከታተል ምንም አይለይም። ሁላችንም ሚና የማንጫወትበት ዋጋ የማንከፍልበት በአድ የሆኑ ነገሮችን ነው እንደራሳችን አድርገን የምንከታተለው። ግን የዜና ፕሮግራሞችን በመመልከት ትምሕርታዊ ቁም ነገር እያደረግን ነው ብለን እራሳችንን እናታልል ነበር!

ዜና መከታተል ግን ከማንኛውም መዝናንያ ትርዒትን ከማየት አይለይም፤ እንደዛው የአዕምሮ ማደንዘዥያ የኑሮ ማምለጭያ ነው። የዜና ትርዒቶች ከተራ ወሬ ሃሜት አሉባልታ ምንም አይለይም ከግብዝነቱ በቀር። ዜና እውነት አስተማሪና ቁም ነገር ነኝ ይላል! ግን ከተከታታይ ድራማዎች ምንም አይለይም። ጭራሽ ይብሳል፤ አብዛኞች የድራማ ትርዒት ትከታታዮች ቁም ነገር ነው ብለው እራሳቸውን አያታልሉም!

ዛሬ ቴለቪዥንም አላይም ዜናም አልከታተልም። በኢንተርኔት አረስቶችን አያለሁ ግን ከተለመዱት የዜና ድረ ገልጾች አይደለም። እርግጥ ነው አንዳንዴ ጽሁፉ አይቼ ይስበኛል እስቲ ጠልቄ ላንብብ እላለሁ ግን እራሴን አቆማለሁ።

ሆኖም ከኢንቴርነት ነው «ዜና መከታተል ያጃጅላል» የሚለውን ጽሁፍ ያገኘሁት። አንብቡት። አልፎ ተርፎ የዜን ፕሮግራሞች አትከታተሉ። በተለይ ሲኤንኤንን (CNN) መቼም አትመልከቱ። ካላችሁበት ቦታ በቴለቪዥን ላይ ካያችሁትም ሮጣችሁ ሽሹ! እራሳችሁን ከአዕምሮአዊ «ቅኝ ግዛት» አድኑ። ቴለቪዥን የምታዩበትን ትርፍ ጊዜአችሁን ከጎረቤታችሁ ጋር በመጫወት አውሉት። እናንተንም እርሱንም እጅግ ይበልጥ ይጠቅማችኋልና።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!