Friday, 22 February 2019

የለገጣፎ «ህገ ወጥነት» የማን ነው?

ሰዎች ከለገጣፎ ገበሬዎች ጋር የውስጥ ውል ተፈራርመው መሬት ገዙ። የእርሻ መሬት መሸጥም መግዛትም ስለማይፈቀድ ይህ ሺያጭ ህገ ወጥ ነበር። ሆኖም ተካሄዷል።

እነዚህ አይነት ሺያጮች ሲካሄዱ የአካባቢው የኦህዴድ (ኦዴፓ) ሹማምንቶች መጀመርያ እንዳላዩ ሆኑ። ቀጥሎ የምዝበራ እድል አይተው ገቡበት። ከገበሬ እየገዙ አትርፈው መሸጥ ጀመሩ። ከገበሬዎች ገዝተው ቤት የሰሩትን ሰዎች ጉቦ ካልሰጣችሁን እናባርራችኋለን፤ መብራት ውሃ እንከለክላችኋለን ወዘተ እያሉ አስፈራሩ። በዚህ መንገድ እራሳቸውን ሃብታም አደረጉ።

የኦዴፓ ላይ ድርስ ያሉ ባለስልጣናት ይህ አይነት ነገሮች አዲስ አበባ ዙርያ እንደሚካሄድ ያውቃሉ። ለነገሩ ሁላችንም እናውቃለን።

ስለዚህ ማን ነው ህገ ወጥ?! መሬት የገዙት ሰዎች? መሬት የሸጡት ገበሬዎች? የመዘበሩ እና በጉቦ ሃብታም የሆኑት የመንግስት ሹማምንቶች? ይህ እንደሚከሰት እያወቀ ዝም ያለው የኦህዴድ አመራር?

ግልጽ ነው፤ በፈቃደኝነት የተስማሙት ሳጭ እና ገዦች በአንጻሩ ንጹህ ናቸው። ማንንም አልጎዱም። ገበሬዎቹ የራሳቸውን መሬት በፈለጉት ዋጋ ሸጡ፤ ገዦችም በተስማሙበት ዋጋ መሬት ገዙ። ይህ ሺያጭ ባይካሄድ የኦህዴድ ሹማምንቶች የገበሬዎቹን መሬት በማይገባ ትንሽ ካሳ ነጥቀው ለኢንቬስተር በውድ ዋጋ እና ጉቦ ሊዝ ያረጉት ነበር።

እነዚህ የኦህዴድ ሹማምንት እና መሪዎች ናቸው ዋና ህግ ወጦች። አዲሱ አረጋ እንዳሉት «ህግ ይከበር» ከሆነ በመጀመርያ ደረጃ የኦህዴድ ሹማምንቶች ነበር መፈተሽ እና መታሰር የነበረባቸው። ሌሎቹ፤ ገንዘብ የተቀበሉት ገበሬዎቹ እና መሬት የገዙት ሰፋሪዎቹ በለዘብተኛ መልኩ መስተናገድ ነበረባቸው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!