ደርግ የ«ከበርቴን» ቤተና ንብረት ሲቀማ በምቀኝነት ተሞልተን አጨበጨብን። እርግጥ ነው አንዳንዱ አላግባብ ብዙ መሬት ይዞ በተከራዮች ይጫወት ነበር። ግን ሌሎች ትንሽ ንብረት የነበራቸው ነበሩ በዚሁ መአበል የተጥለቀለቁ። የሚያከራዩት ሶስት አራት ቤቶች ሲወረሱ ባዶአቸውን ቀሩ። ማንም አላዘነላቸውም። «እንኳን ተነጠቁ» ብለን የጅምላ ፍርድ ላይ ነበርን።
በህወሓት ዘመን ደግሞ ለ«ልማት» እና «ኢንቬስትሜንት» ተብሎ የበርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ንብረት በምንግስት ተነጥቋል። አንዳንዱ ባዶውን ቀረ። አንዳንዱ እጅግ አነስተኛ ካሳ ተሰጥተው። ሌላው ከከተማ ውጭ ባዶ መሬት ላይ ተወረወረ። ይህ ሁሉ ሲከሰት የአዲስ አበባ ህዝብ (በጅምላ ለማውራት) ምንም አላደርገም። እርግጥ መጮህ እና መደራጀት ሊያሳስር እና ሊያስገድል ይችል ነበር። ግን ገንዘብ ሰብስቦ ለተፈናቀሉ ተጎጂዎች መስጠት ምንም ቅጣት አያስቀጥልም ነበር። ከኔ ጀምሮ አንዳችን ይህን አላደረግንም። የባለንጀሮቻችንን ህምም ዝም ብለን ተመለከትን።
ዛሬም እንዲሁ። ለገጣፎ የሚኖሩ ወንድም እህቶቻችን ቤቶቻቸውን እያጡ እያለ ከመጮ ሌላ ምንም አናደርግም። አንረዳቸው፤ አንደራጅ። ትንሽ ጉዳዩ ያናደደን ካለን መንግስት ላይ ጣታችንን እንጠቁማለን!
ከዛ ይልቅ እራሳችን ላይ ነው መፍረድ ያለብን። የአዲስ አበባ ህዝብ ለባለንጀራው በአግባቡ ቢራራ እስካሁን ተደራጅቶ የህ አይነት ግፍ እናይከሰት ማድረግ ይችል ነበር (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2019/02/blog-post_22.html)። ግን አላደረገውም፤ አላደረግነውም።
ስለዚህ ጥፋቱ በዋነኝነት የኛ የአዲስ አበባ ህዝብ ነው። ጣቶቻችንን ሌሎች የማይሰሙን ላይከመጠቆም ስራችንን ሰርተን ተደራጅተን እርስ በርስ ብንጠባበቅ ለሁሉም፤ ለጎጂዎቻችንም ለመላው ሀገራችንም፤ ጠቃሚ ነበር። ለችልተኛችን ንስሃ ገብተን ወደ ስራ እንግባ። ሌላ መፍትሄ የለም!
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!