የሰላም ክፍሌ ይትባረክ ብሎግ፤ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለኝን ትናንሽ ሀሳቦች በትህትና አቀርባለሁ። ለስሕተቶቼም በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ
Wednesday, 13 February 2019
የንስሐ ፖለቲካ በአሜሪካ
በአሜሪካ ይሁን በሌሎች ምዕራባዊ ሀገራት የንስሐ ፖለቲካ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/blog-post_30.html) የተለመደ አይደለም። ፖለቲከኞች የእውነት ይቅርታ ብዙ ጊዜ አይጠይቁም። ይቅርታ ከጠየቁም ለጋራ ወይንም ለሀገር ጥፋት ነው እንጂ እራሳቸው ላደረጉት ስለራሳቸው ይቅርጣ አይጠይቁም። አልፎ ተርፎ ይቅርታ ከጠየቁ የፖለቲካ ጥቅም ካለው ብቻ ነው።
የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዋልተር ጆውንዝ (Walter Jones) ግን የተለዩ ፖለቲከኛ ነበሩ (https://www.theamericanconservative.com/articles/walter-jones-cried-while-the-rest-of-them-lied/)። ዋልተር ጆውንስ እንደ ሁሉም የሪፐብሊካን ፓርቲ ፖለቲከኞች እና አብዛኞች የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፖለቲከኞች የጆርጅ ቡሽ የኢራቅ የ2003 (እ.አ.አ) ወረራን ደግፈው ነበር። በ2001 በአሜሪካ ላይ የተፈጸመው ሽብር በኋላ የአሜሪካ ህዝብም ፖለቲከኞች ማንኛውም «ጸረ ሽብር» ጦርነትን ይደግፉ ነበር። ዋልተር ጆውንስ በዚህ በኩል አልተለዩም፤ ጭራሽ ጸንፈኛ አቋም ይዘው ነበር። የፈረንሳይ መንግስት ወረራውን አልደግፍም ሲል ጸረ-ፈረንሳይ እርምጆችን ደገፉ። ዋልተር ጆውንስ የሚወክሉት ወረዳ በጣም ጦር ሰራዊት እና ጦርነት የሚደፍግ ህዝብ ያለበት ቦታ ነበር እና አቋማቸው ይህንን አንጸባረቀ።
የአሜሪካ ወታደሮች እበጦርነቱ መሞት ሲጀምሩ እና ዋልተር ጆውንስ ሬሳዎቻቸውን በየቀኑ እና በየሳምንቱ ማየት ሲጀምሩ የ«ጦርነት ወዳጅ» አመለካከታቸውን ተመልሰው ማየት ጀመሩ። ስህተታቸውን ተረዱ። ተጸጸቱ። ወደ ንስሐ ገቡ። እስኪሞቱ ድርስ በተደጋጋሚ ይቅርታ ጠየቁ። ለያንዳንዱ ሃዘኝነቶች የይቅርታ ደብዳቤ ጻፉ! 11,000 ደብዳቤዎች ጻፉ። ደጋግመው ይቅርታ ጠየቁ። አለቀሱ። «ጦርነቱን በመደገፌ 4,000 በላይ አሜሪካኖች እንዲሞቱ አድርጊያለሁ» ብለው ተናገሩ። ለስህተታቸው ምንም ሰበብ አላረጉም። ያደገቱን «ስህተት» አላሉትም፤ «ኃጢአት» ነው ያሉት።
የዋልተር ጆውንስ ንስሐ የካቶሊክ እምነታቸውን እውን በማድረጋቸው እና በተግባር እይሚያምኑ እንደሆነ ያሳያል ይባላል። የሰው ልጅ ክቡር ነደሆነ ተረድተው ምንም ፖለቲካ ከሰው ልጅ እንደማይበልጥ ገባቸው። ሰው ቁጥር ወይንም መሳርያ ሳይሆን የእግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ተረዱ። የአሜሪካ የጦር ኢንዱስትሪ፤ የፖለቲካ ድጋፍ፤ የእስራኤል «ትቅም»፤ ገንዘብ፤ ወዘተ ከሰው ልጅ እንደማይበልጥ ከልባቸው ተረዱ። ለዚህም ይመስላል ጦርነቱን መደገፋቸው እንዲህ ያጸሰታቸው።
ዋልተር ጆውንስ በወሰዱት አቋም ምክንያት ስራቸውን ሊያጡ በጥቂት ተረፉ። ግዙፍ የፖለቲካ ኃይሎች፤ ሎቢዎች፤ እና የራሳቸው የሪፐብሊካን ፓርቲ ዋልተር ጆውንስ በእጩነትም በመርጫም እንዲሸነፉ በዙ ብር አወጡ። አልሆነላቸውም። ዋልተር ጆውንስ ሁለት ቀን በፊት ከዚህ ዓለም ሲለዩ የምክርቤት ወንበራቸውን እንደያዙ ነው የሞቱት።
የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዋልተር ጆውንስ ለሁሉም ፖለቲከኛም ብዙሃንም ታላቅ ምሳሌ ናቸው። ነፍስ ይማር።
እዚህ ላይ እኔም አንድ ንስሐ ልግባ። እኔም በወክቱ የኢራቅን ወረረ ደግፌ ነበር። አሜሪካ ለመቶ ዓመታት አምባገነኖችን ይህን ማንንም የሚጠቅማቸውን እየደገፉ ዛሬ አምባገነኑ ያውሩዱ በሚል እጅግ ደካማ አስተሳሰብ ወረራውን ደገፍኩኝ። ግን ዋና የአስተሳሰቤ ድክመት ፖለቲካን አለመረዳት አይደለም። የሰው ልጅ ማንነቱ ስላልገባኝ ነው። ጦርነት ለኔ ሃሳብ (abstract) ብቻ ነበር። የክፉ መንፈስ ማስተናገጃ እንደሆነ አልቆጠርኩትም። ሰዎች እንደሚሞቱ ባስቅም ብዛው ደረጃ አላውቅም ወይንም አይገባኝም ነበር ማለት ይቻላል። የሰው ልጅ በእግዛአብሔር ምሳሌ በመፈጠሩ ዘንድ ማንኛውም የሰው ልጅን የሚጎዳ እና የሚገል ነገር መቃወምን ግድ ነው። «ሄዶ ይዋጋልኝ (ን)» ማለት እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው። ከሩቅ ሆኘ ለሆነ abstract ሃሳብ ሰው ይሙት ማለት የሰው ልጅ ማንነቱን አለማወቅ እና ሰውን በተዘዋዋሪ መግደል ማለት ነው።
እርግጥ እኔ አንድ ግለሰብ ነኝ። እንደ ዋልተር ጆውንስ የኢራቅ ወረራ እንዲካሄድ የመረጥቁኝ ወይንም የውሰንኩኝ አይደለም። ግን ሃሳቡን በመደገፌ ከሳቸው ምንም እንዳልለይ ያደርገኛል። «ለቀደሙት። አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። 22 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤» (የማቴዎስ ዎንጌል 5:21,22) በሃሳብ የተፈጸመ ኃጢአት ከተገበረ ኃጢአት ብዙ አይለይም።
የዚህ ትምሕርት ምንድነው? ፖለቲካ ሆኖም ሌላ ነገር ከሰው ልጅ በላይ ካደረግን ሁልጊዜ ወደ ክፋት ነው የምንሄደው። ፖለቲካን ከእግዚአብሔር እና ቃሉ በላይ ካደረግን፤ ፖለቲካን ጣኦት ካደረግን ሁልጊዜ ወደ ክፋት ነው የምናመራው። ስለዚህ ሁሉ አቋሞቻችንን በትህትና እናስተናግድ። ራሳችንን ሁልጊዜ እንመርምር። ሁሌ የሰው ልጅን ማንነት እናስቀድም።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!