Monday, 1 April 2019

የህፃንነት ፖለቲካ

ላለፉ 50 ዓመታት፤ ከደርግ አቢዮት ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጎራው በህፃንነት የፖለቲካ አስትሳሰብ ተለክፏል። ተመልከቱ...

በአንድ በኩል ኃይል ያለው የጎሰኛ ጎራ አለ። ኃይል ማለት ኃይለ ቃል አይደለም አንዳንዶች ሁለቱ አንድ ይመስላቸዋልና። «ከተሳደብኩኝ ተሟገትኩኝ» ብሎ የሚያስብ አለ እንጂ። ኃይል ማለት ጎሰኛው በየ መንግስት መዋቅሩ ተሰግስጓል። ገንዘብ አለው። ሚዲያ አለው። መዋቅሮች አለው። ጦር አለው። አካላዊ እና ንብረታዊ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ፍላጎቱን በተለያየ መንገዶች ሊያስፈጽም ይችላል። መንግስት ውስጥ የተሰገሰገው በዛ አቅሙ ይጠቀማል። ጦር ያለው በሱ ይጠቀማል። ሚዲያው እንዲሁ። «ኃይል» ማለት ይህ ነው። ጎሰኛው ተጨባጭ (tangible) ኃይል አለው።

የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ወይን አንድነት ጎራው ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ኃይል የለውም። መንግስት መስሪያቤት ውስጥ ያለው ቁጥሩ ትንሽ ነው መንግስት የኢህአዴግ ስለሆነ። ጦር የለውም። ሚዲያው ደካማ ነው። ምንም መዋቅር የለውም። ገና እየተደራጁ ያሉ እነ ግንቦት 7 እና ባልደራስ ነው ያሉት። ሌላ ነገር የለም። ሰለዚህ ይህ ጎራ ፍላጎቱን ለማስፈጸም አቅም የለውም። የራሱን መከላከልም አቅም የለውም። መዋቅር እና ኔትወርክ አልዘረጋም። ከሞላ ጎደል ኃይሉ እጅግ አነስተኛ ነው። አልፎ ተርፎ ይህ ጎራ ዋናው hobbyው እርስ በርስ መጠላለፍ እና መጣላት ነው።

ይህ እንደሆን እነ ጠ/ሚ ዓቢይ የሚፈሩት ማንን ነው፤ ጎሰኛውን ነው የኢትዮጵያ ብሄርተኛው? ጎሰኛውን ነው። ገጀራን ዝም ብለው ባልደራስን የሚተቹት ለምንድነው? ባለ ገጀራው ኃይል አለው ባልደራስ የለውም። ግልጽ ነው።

በዚህ ሁኔታ ጠ/ሚ ዓቢይ ላይ መውረድ ምን ዋጋ አለው?! ቢፈልግም ገጀራውን ዝም ብሎ መደምሰስ አይችልም። በዘዴ መሆን አለበት፤ ጊዜ ይፈጃል። እያሳሳቀ ነው ሊያጠፋው የሚችለው። አንዳንዶች እንደሚሉት ከባለ ገጀሮቹ አንዱ ከሆነ ጠ/ሚ ዓቢይ መነጫነጫችን ዋጋ የለውም ማለት ነው።

መፍትሄው አንድ ብቸኛው ነው፤ የአንድነት ኃይሉ «ኃይል» ማጠራቀም አለበት። ከባለ ገጀራው እጥፍ ኃይል ከሌላው ዋጋ የለውም። ይህን ኃይል እስኪያጠራቅም ደግሞ ወደ ጸብ መግባት የለበትም፤ ይህ ቀላል የፖለቲካ ስልት ነው። አንገት ደፍቶ ሁሉንም እንደ አጋር አስመስሎ የኃይል ማጠራቅም ስራውን መስራት አለበት። እንጂ ገና ምንም ኃይል ሳይኖረው ሌሎችን አምበረግጋለሁ ማለት እራስን መጥለፍ ማለት ነው።

ስለዚህ ጠ/ሚ ዓቢይ ላይ የምትወርዱበት፤ ጩሀታችሁ ዋጋ የልውም፤ ጭራሽ ዋጋ ያስከፍላል። እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ተጨባጭ ኃይል እስኪኖረን እሱ ላይ መጮህ፤ እርስ በርስ ጸጉር መሰንጠቅ ዋጋ የለውም። መጀመርያ ተደራጅተን መዋቅሮች እና ኔትዎርኮች ዘርግተን ከዛ ብኋላ ወደ ሙግት።

(ለምን «ባለ ገጀራ» የሚለውን አሉታዊ አነጋገር ተጠቀምኩኝ? የዚህ ጽሁፍ audience የጎሳ ብሄርተኞች ላይ ኃይለ ቃል የሚጠቀሙ የአንድነት ሰዎች ናቸው። ለአንባቢው የሚመች ቃላቶችን ተጠቀምኩኝ። እነ ለማ መገርሳ ለርዥም ዓመታት «ኦነግ በሽፋን» የሆነውን የኦህዴድ ካድሬዎችን ሲያነጋግሩም እንዲሁ ብትረዷቸው ጥሩ ይመስለኛል።)

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!