Showing posts with label የኢቶጵያ ብሄርተኝነት. Show all posts
Showing posts with label የኢቶጵያ ብሄርተኝነት. Show all posts

Friday, 23 September 2016

የአማራ የፖለቲካ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ህልውና እጅግ አስፈላጊ ነው

2009/1/12 .. (2016/9/22)

ከተለያዩ ጽሁፎች እንደጠቀስኩት ለላእፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢሚዛናዊ ሆኗል። በ1983 ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ (Ethiopian nationalist) የፖለቲካ መሪዎች ለ40 ዓመታት እርስበርስ በመፋጀት እራሳቸውን ጦራቸውንም አጥፍተው ነበር። ስለዚህ የሀገሪቷ ህገ መንግስት የተቋቋመው ሀገሪቷም የተስተዳደረችው በጎሳ ብሄርተኛ (ethnic nationalist) የሆኑ ፖለቲከኞች ነው። የፖለቲካ ኃይል በጠቅላላ በጎሳ ብሄርተኝነት እጅ ነው።

በዚህ ምክንያት በርካታ የሆነው የሀገር ብሄርተኛ ህብረተሰብ በፖለቲካ ዙርያ አልተወከለም። ለዚህ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢሚዛናዊ ነው ማለት የሚቻለው፤ የጎሳ ብሄርተኞች ከመጠን በላይ ውክልናና ድምጽ አላቸው ርዓዮት ዓለማቸውንም ያራምዳሉ፤ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ግን አልተወከሉምም ድምጻቸውም የሚገባው ያህል አይሰማም። ይህ ሁኔታ ነው ዛሬ በኢትዮጵያ የሚታየውን ከፍተኛ ጎሰኝነትና ዘረኝነት ያመጣው።

ጎሰኝነቱ ለሀገሪቷ ህልውና እጅግ አደገኛ መሆኑ ዛሬ ግልጽ ሆኗል። ለዚህ ያለን አንዱ ከባድ መረጃ የጎሳ ብሄርተኛው ፓርቲ ኢህአዴግን ምን ያህል በሁኔታው መስጋቱ ነው። ከኢህአዴግ አመራር መካከል ጎሰኝነት በሀገሪቷ ፖለቲካ በዝቶ ለስልጣናችንም አስጊ ስለሆነ ፓርቲያችንን ወደ አንድ የሆነ በጎሳ ያልተከፋፈለ ፓርቲ (ብአዴን ህውሃት ኦህዴድ ቅርቶ ማለት ነው) እንቀይር እያሉ ይገኛሉ። ሀገሪቷን ከዚህ አደጋ ለማውጣት የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራ የፖለቲካ ድርሻውን በድፍረት (25 ዓመታት እንቅልፍ በኋላ) መውሰድ አለበት።

እሺ ማን ናቸው የኢትዮጵያ ብሄርተኞቹ? ባሁኑ ዘመን ከበየ ክልሉ ቢገኙም በርካታዎቹ ከጎሳዊ ውህደት ያለበት ስፍራዎች እንደ አዲስ አበባና ሌሎች ትላልቅ ከተማዎች ይገኛሉ። በክልል ደረጃ ደግሞ ጠቅላላው የአማራ ክልል የሀገር ብሄርተኛ ነው። ይህንን እውነታ በምርጫ 1997 ቅንጅት ያሸነፈበት ቦታዎች መረዳት እንችላለን። ለማስተዋስ ያህል ኢህአዴግና ህብረት የጎሳ ብሄርተኝነት የሚበዛበት ቦታዎችን አሸነፉ፤ ቅንጅት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚበዛበትን ቦታዎች አሸነፈ።

የሚቀጥለው ጥያቄ እንዴንት ነው ይህ ከሀገር ፖለቲካ የጠፋው የሀገር ብሄርተኛ ጎራ የሚገባውን ፖለቲካዊ ድርሻ መያዝ የሚችለው። በመጀመርያ ከታች ከመላው ህብረተሰብ (grassroots) ጀምሮ የአንድነትና የአንድ አላማ መንፈስ ልያድርበት ይገባል። ይህ ለማንኛውም ስኬት ቀድመ ሁኔታ ነው! ሰውው እንደዚህ «አንድ ልብ» ሲሆን ነው የፖለቲካ እርምጃዎች መውሰድ የሚችለው። በዛሬው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ህብረተሰቡ ማድረግ የሚችለው እንደነዚህ አይነት ነገሮች ነው፤ በተለያዩ መዋቅሮች (የመንግስት መስሪያቤቶች፤ የሰራተኛ መሐበራት፤ የገበያ መሐበራት፤ የተቃራኒ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ ኢህአዴግ፤ ወዘተ) ስርጎ መግባትና መቆጣጠር፤ የእምቢተኝነት እንቅስቃሴዎች፤ ሰላማዊ ሰልፎች፤ ወዘተ።

የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እነዚህን እርምጃዎች ማካሄድ ይችላሉ ወይ? እንደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተማዎች የተለያዩ አይነት ሰዎች ስለሚኖሩባቸው፤ ከተማ በመሆኑ የመሐበራዊ ኑሮ ውስን ስለሆነ፤ ሰውዉ በደምብ ስለማይተዋወቅ፤ የመንግስት ደህንነት አትኩሮ ስለሚከታተላቸው፤ ወዘተ እንድዚህ አይነት ስራዎች ለማኮናሆን ከባድ ነው።

በአማራ ክልል ግን እነዚህ ችግሮች የሉም ወይም ያንሳሉ። ህዝቡ ባብዛኛው ለትውልድ የሚተዋወቅ ነው፤ አብዛኛውም ከገጠር ነው የሚኖረው። በደህንነት በኩልም መንግስት ብዙ አማራጭ የለውም። ኢህአዴግ በሀገሩ በአማራ ደህንነቶች ልቆጣጠር ካለ ይከዱታል። አንድ ልብ ማለት ይህ ነው፤ የገዛ ወንድሙንና ዘመዱን አያጠቃም። ከማጥቃት ፋንታ ለአዲስ አበባ ላሉት አዛዦቹ እያስመሰለም ቢሆን ከሀገሩ ህብረተሰብ ዘመዱ ጋር ይቆማል። ደህንነት አስፈጻሚዎቹን ከውጭ ክልሎች ላምጣ ከለ ደግሞ መንግስትን የሚያናጋ ጠባሳ የሚያመጣ የጎሳ ጦርነትን ይጋበዛል። ስለዚህ ህዝቡ ከተባበረ ከተማመነም «አንድ ልብ» ከሆነም ከሃዲዎቹም ውስን ከሆኑ የመንግስት ደህንነት ምንም ማድረግ አይችልም። በዚህ ምክንያቶች የአማራ ንቅናቄ ስኬታማ መሆን እድሉ ከፍ ያለ ነው።

የአማራ ንቅናቄ ተሳካ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች የፖለቲካ ኃይል በሚገባው ጨመረ ማለት ነው። ከሀገሪቷ ሁለቱ ትላልቅ ክልሎች አንዱ ከጎሳ ብሄርተኛው ኢህአዴግ እጅ ወጣ ማለት ነው። ስኬቱም እንደ አዲስ አበባ አይነቱን የኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሚበዛበት ቦታዎች እንዲነሱ ይገፋፋል። ቅድም እንደጠቀስኩት ደግሞ ይህ የሀገር ብሄርተኛ ኃይል ሲጨምር የሀገሪቷን እሚዛናዊ የሆነውን የፖለቲካ ሁኔታ ወደ መስተካከል ይመራዋል። የጎሳ ፖለቲካ ያስፋፋውን ለሀገሪቷ አስጊ የሆኑትን ጎሰኝነትና ዘረኝነትንም እንድንቆጣጠርና እንድንቅንስ በሩን ይከፍታል። ባጭሩ ቢዝህ ምክንያት ነው የአማራ የፖለቲካ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ ህልውና እጅግ አስፈላጊ የሆነው።

Wednesday, 21 September 2016

«ወያኔ» እኛው የወለድነው ልጅ እንደሆነ አንካድ!

2009/1/11 .. (2016/9/21)

የጽሁፎቼ ሁሉ ዋና አላማ ለኢትዮጵያ ችግሮች ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አኳያ መፍትሄ ለማጋኘት ነው። ስሜት ለማተንፈስ፤ ለመሳደብ፤ በባዶ ቤት ለመዛት ወይም ለመለመን አይደለም። መፍትሄ መፍትሄ መፍትሄ ነው አላማዬ። የአንድ ችግር መፍትሄ ለማግኘት ደግሞ ምንጩን ማወቅ ግድ ነው። ምንጩን ካወቅን መፍትሄው ይመጣል።

«ወያኔ» እኛው ሀገር ወዳድ ነን የምንለው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኞች የወለድነው ልጅ እንደሆነ ከገባን ምን ስህተሀቶች አድርገን ልጃችን እንደዚህ እንደሆነም እነዚህንም ስህተቶች እንዴት በመአረም የኢትዮጵያ ጠክላላ የፖለቲካና መሐበራዊ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደምንችል እንረዳለን።

የኢትዮጵያ ዋና የፖለቲካ ችግርን በቀላሉ ማስቀመጥ ይቻላል፤ ያለው መንግስት በቂ ኢትዮጵያዊያንን አይወክልምም መላው ህብረተሰቡም በአንድ ሀገራዊ ውል (የሀገሪቷ ፖለቲካ ምን መምሰል እንዳለበት – social contract) አልተስማማምም።

ሁላችንም እንደምናውቀው ኢህአዴግ በህወሃት ትጽዕኖ የሚገዛ ድርጅት ነው። ርዓዮት ዓለሙም በጎሳ ብሄርተኝነት የተመሰረተ ነው። ከዚህ «ስዕል» ማን ነው የሚጎለው? ወይም ከሀገራችን ፖለቲካ የትኛው በርካታ ህዝብ የሚወክል ጎራ ነው የጠፋው? ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ነኝ የሚለው ጎራ ነው የጠፋው። እንዴት እንደዚህ አይነት አገዛዝ በኢትዮጵያ ሊሰፍን ቻለ?! ከሌሎች ጽሁፎች እንደጠቀስኩት የኢትዮጵያ ብሄርተኞች በኃይለ ስላሴም በደርግም ዘመን የራስ ማጥፋት ዘመቻ ስላካሄዱ ነው። የኃይለ ስላሴ መንግስት እንደ መሬት ለአራሹ አይነት አስፈላጊ ለውጦች ባለማድረግና በኢትዮጵያዊነት ፋንታ ዘመናዊነትን እከተላለሁ ብሎ ሀገር አፍራሽ የሆነ የተማሪ ንቅናቄ የሚባል ትውለድ አፈራ። ደርግን ሻእብያን ህወሃያትን ኦነግን ኢህአፓ ወዘተ አፈራ። 1983 ሲደርስ እራሱን በደምብ አጥፍቶ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የገዢ ወገን በጎሳ ብሄርተኛ ብቻ ሞልቶ ቀረ። ለዚህ ነው ዛሬ ያለነው ሁኔታ የተፈጠረው እንደዚህም ነው ህወሃት ተፈጥሮ ያደገው።

ላለን ችግር ታድያ ምክንያቱ በመጀመርያ ህወሃት ነው? በፍጹም። ህወሃትም ኢህአዴግም እኛ በቀደድንላቸው ግዙፍ ቀዳዳ ባላቸው የመንፈስና የጭንቅላት አቅም የሚችሉትን እያደረጉ ነው። ከነሱ እስከ ዛሬ ያደረጉት በላይ መጠየቁ አግባብ አይደለም።

እስቲ ስሜታዊ ሳንሆን ተረጋግተን እናስበው፤ ኢህአዴግ ኢትዮጵያን እገዘዋለሁ ብሎ በፍጹም አስቦ አያውቅም። ኃይላችን ውስን ነው፤ የመኻል ሀገር መንግስቱ በርካታ ኃይልና አቅም አለው፤ ብሎ እንኳን ህወሃት ከሱ ጠንካራውም ሸአብያ ደርግን ከማሸነፍ ድርድርን በበር የሚያስበው። ህወሃት አሸንፎ ሙሉ ሀገሪቷን ሲገዙ ዱብዳ ነው የሆነባቸው።

በተፈጥሮ ትዕቢትን ይጨምራል። ኢህአዴግ ደግሞ እንደ ዳዊት ታላቁን ኃይለኛ ጎሊያድን ያሸነፈ ስለመሰለው ይበልጥ ኩራትና በራስ መተማመን አደረበት። ይህን ግብ መምታት መቻሌ ድርጊቴ በሙሉ ትክክል ነው ማለት ነው ብሎ ማሰብ ጀመረ። እራሱንም ከሌሎች ድርጅቶች በሙሉ ልዩ ጎበዝና የበላይ አድርጎ ማሰብ ጀመረ። ህወሃት በዚህ መንፈስ ነው በ1983 ስልጣን የያዘው።

ከዛ ቀጥሎ ስልጣኑን በሚያረጋግጥበት ሰሞን ተቀናቃኞቹ አንድ በአንድ ሲፈርሱ አየ። ኦነግን በቀላሉ አሸነፈ። ኢህአፓም ሌሎችም እንደዚሁ። የኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ የፖለቲካ ጎራ ደግሞ ጭራሽ ምንም ኃይል ስላልነበረው ኢህአዴግ ምንም ማድረግ አላስፈለገውም።

በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት የፖለቲካ ጎራ በዛን ጊዜ ኃይል ማጣቱ ኢህአዴግን እጅግ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል። ኃይል ስላጣ ከጥቂት የሆኑ የተማሩ ወገኖች በስተቀር ይህ ጎራ ከህብረተሰቡ ምንም ድጋፍ የለውም ብሎ ኢህአዴግ ገመተ። የቀዝቃዛ ጦርነት፤ የደርግ የኮሙኒስት አቋም፤ የኤኮኖሜው መበላሸት፤ ወዘተ እንደ ምክንያት ሳይቆጠር ደርግ መሸነፉ ኢትዮጵያ ብሄርተኝነት እንደተሸነፈም ብሀገሪቷም እንደማይፈለግ ተቆጠረ። ይህ ታልቅ ስህተት መሆኑን ኢህአዴግ በየጊዜው እየገባው ሄዷል።

ዞሮ ዞሮ ኢህአዴግ ሀገሪቷን ተቆጣጠረ። ማንም አልተፎካከረውም። ትዕቢቱም እየጨመረ ሄደ!

ኢህአዴግ ስልጣኑን ካረጋገጠ በኋላ ህዝቡ አልፎ አልፎ መንግስት ላይ መነሳት ጀመረ። ኢህአዴግ ሁሉንም አይነት አመጽ (ለምሳሌ የ1986ና የ1993) በቀላሉ ተቆጣጠረ። ትዕቢቱ መጨመሩ ቀጠለ።

በዚህ ጊዜም አንዳንድ ተቃዋሚ ድርጅቶች ቢያንስ መንግስትን ለመተቸት ያህል ይበቁ ነበር። ግን እርስ በርስ ሲጣሉና በትንሽ ግፊት ሲፈርሱ ሲያይ የኢህአዴግ ትዕቢት ማየል ቀጠለ።

ከዛ ቀጥሎ የኤርትራ ጦርነት ተነሳ። ኢህአዴግ ይሄንንም ፈተና እንደ ድርጅት ቆስሎም ቢሆን 70,000 በላይ ወታደር ሞቶም ቢሆን አሸነፈ። የሚፈራውን ታላቅ ወንድሙን በማሸነፉ የዝቅተኛ መንፈሳቸውን አስወገዱ። ኢትዮጵያንም ለብቻው ተቆጣጠረ! ትዕቢቱም ጨመረ። እኛ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኞች ከዳር ሆነን አጨበጨብን።

አምስት ዓመት በኋላ ኢህአዴግ የምርጫ 1997 ፈተና አጋጠመው። ፈተናው እጅግ ከባድ ቢሆንም በመጨረሻ ኢህአዴግ ያለውን የተቃዋሚ ጎር ድራሹን አጥፍቶም የሀገሪቷን ኤኮኖሚ ክፍ አድርጎ ተቃውሞን ገደለው። ለዚህ ሁሉ ድል እራሱን ለመሸለም ያህል የ2007 ምርጫን መቶ በመቶ እንዲያሸንፍ አደረገ። ትዕቢቱ ናረ!

ይህንን ታሪክ ስንመለከት እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ህወሃትን እንደፈጠርነው፤ አጣመን እንዳሳደግነው፤ ጥሩ ምሳሌ ባለመሆናችን እንዲክደን ያደረግነው፤ እራሳችንን በማጥፋት ልቅ እንዳደረግነው ሁሉ ማመን አለብን። ኢትዮጵያ በኛ እጅ ሆና ደጋግመን ተሳሳትን አጠፋን ጨኮንንም አበላሸንም። ለእነ ህወሃት መንገዱን ጨርቅ አደረግንላቸው።

ስልጣን ከያዙም በሗል ጠፋንባቸው። እርስ በርስ ያለመተባበርም የመጠራጠርም ብሽታ ይዞን እነሱን የሚፎካከር የፖለቲካና ህዝባዊ ኃይል መዋቀር አልቻልንም። ይህም ኢህአዴግ የተሳሳተ መንገዱን እንዲቀጥል ረዳው ብቻ ሳይሆን አስገደደውምም ማለት ይቻላል። አንድ ድርጅት እራሱን ለማስተካከል ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ተግባራው ምክንያት (incentive) ያስፈልገዋ። ኢህአዴግም የሚቀናቀነው ኃይል ፊቱ ቢቆም ኖሮ የተሻለ ሃሳብን እንዲያሰላስል ይገደድ ነበር። እኛ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኞች ግን ይሄንን ትንሽ ግዴታችንንም አላሟላንም።


ታድያ ሀገራችን የፖለቲካ ችግር ምንጭ ዬት ነው? ከኛ ከኢትዮጵያዊ ብሄርተኞች ነው። መፍትሄውም ከኛ ነው። ኢህአዴግን መክሰስም መፍትሄ ከሱ መጠበቅም ዋጋ ዬለውም። እኛ ነን ችግሩን ያመጣነው እኛም ነን የምንፈታው። ከፈታነው በኋላ ልጆችንን «ወያኔን» ይቅርጣ እንጠይቀዋለንም።


Thursday, 15 September 2016

በፈቃዳችን ነው የምንገዛው

2009/1/4 ዓ.ም. (2016/9/14)

ይህን ነጥበ በተደጋጋሚ በተለያየ መንገድ ለማስረገጥ እወዳለሁ። የዛሬው የኢህአዴግ አገዛዝን የኢትዮጵያ ህዝብ አይፈልገውም የምንለው የዚህ አባባላችንን ሙሉ ትርጓሜ ልንረዳ ይገባል። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ኢህአዴግን የማይፈልግ ከሆነ ኢህአዴግ የአናሳ ሰዎች አገዛዝ ነው ማለት ነው። አናሳ ድጋፍ ያለው መንግስት ያለ የሌላው ፈቃደኝነት ሊገዛ አያችልም። ልድገመው፤ የአናሳ ድጋፍ ያለው መንግስት ያለ ሌላው ፈቃድ ሊገዛ አይችልም! 

ስለዚህ «የኢህአዴግ አገዛዝን የኢትዮጵያ ህዝብ አይፈልገውም» ስንል የምንገዛው በገዛ የራሳችን ፈቃደኝነት በራሳችን ጥፋት በራሳችን ድክመት ነው ማለት ነው። ሌላ ትርጉም የለውም። የችግሩ ምንጭም መፍትዬውም ከኛ ነው። ኢህአዴግ እንደ በሩ ክፍት የሆነ ቤት ያገኘ ሌባ ነው። ወደ ቤታችን ብንመለስ ሰተት ብሎ ይለቃል። ታድያ መችሄ ነው ወደ ቤታችን የምንመለሰው?

«ድጋፉ አናሳ ቢሆንም ፖሊሱ ደህንነቱ የጦር ሰራዊቱም በሙሉ ከነሱ እጅ ናቸው» ይባላል የኢህአዴግን ኃይልና ጥንካሬ ለማስረዳት። ለማስረዳት ብቻ ሳይሆን ለድክመታንንና ለሽንፈታችን ምክነያት ለመፍጠር። ኢህአዴግን ለማሸነፍ እጅግ ከባድ መሆኑን ለመግለጽ። እንዲሁም ኢህአዴግ ስልጣን በመያዙ ሃላፊነታችንን ለመሸሽ። 

ግን ለዚህ መልሱ ቀላል ነው። መሳሪያው በማን እጅ ነው? በጣም አብዛኛው ፖሊስና ጦር ሰራዊት አማራ ኦሮሞና ከትግራይ ያልሆኑ ጎሳዎች ናቸው። ይህ ማንም ያማይክደው ሀቅ ነው። የፖሊስና የጦር ስራዊቱ አመራር ብቻ ነው ባብዛናው ህወሓቶች ወይም ትግሬዎች። መሳሪያ ደግሞ በአመራር እጅ ሳይሆን በተራ ወታደሩ እጅ ነው ያለው። ስለዚህ መሳርያው በአማራና በኦሮሞ እጅ ነው ማለት ይችሃላል!

እሺ ጡንቻውን ደግሞ ትተን በመንግስት መስርያቤት አብዛኛው ማን ነው። በዚህም ረገር ትግራዩ አናሳ ነው። ለመደምደም ያህል የኢትዮጵያ ስምንት በመቶ ሆነው የትግራይ ህብረተሰብ አገሩን በሙሉ ሊያስተዳድሩት አይችሉም። ሊያስተዳድሩም ሊቆጣጠሩም ሊከታተሉም አይችሉም።

ሌሎቻችን ሃላፊነታችንን ድክመታችንን ለማምለት ምክነያት ፈልገን «ትግራይ ብቻ ሳይሆን ከሌሎቹ ጎሳዎች አደርባዮች እየረዷቸው ነው» እንላለን። ታድያ አደርባዮቹና ትግራዩ ሲደመር አብዛኛ ነው? ከሆነ ኢህአዴግ አብዛኛውን የሚወክል ጥሩ መንግስት ነው ማለት ነው! ታድያ ነው?አይደለም። በእውነቱ የአደርባዩም ቁጥር ትንሽ ነው።

ታድያ እንዴት ነው ኢህአዴግ የሚገዛው። በሌሎቻችን ፈቃድና ትብብር ነው። ትብብር ማለት እያንዳንዳችን ለዚህ አገዛዝ ያለንን አስተዋጾ ተመልክትን አምነን ከመቀየር ይልቅ «ወያኔ ሴጣን ነው» እያልን ማልቀስ ነው። ለኢህአዴግ ስልጣን ለመያዝ ያለንን ሃላፊነት ማምለጥ የኛ የተቃዋሚ ችግር ላይ ከባዱንና አስፈላጊውን ስራ መስራት እንፈልጋለን። «ወያኔ ሴጣን ነው» ብለን መዝፈን ነው የሚቀለን።

ከአብዛኛው የፖለቲካ ጎራ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነን ኢትዮጵያዊ ብሄርትኞች ነን የምንለው ለኢሃዴግ አገዛዝ ትልቅ ሃላፊነት አለብን። ኢህአዴግን በመጀመርያ የወለድነው እኛ ስለሆንን። በኃይለ ስላሴ ዘመን በቂ ለውጥ ባለማድረጋችን፤ የማይሆን «ፈረንጅ አምላኪ» ትውልድ ወልደን የራስ ማጥፋት ዘመቻ ማድረጋችን፤ የደርግን መንግስት ተቆጣትረን ትክክለኛ መስመር ባለማስያዛችን፤ በቀይ ሽብር እንደገና የራስ ማጥፋት ዘመቻ ማካሄዳችን፤ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው ሻዕብያ ኢህአዴግና ኦነግ በ1983 የኢትዮጵያን ህልውና ብቸኛ ወሳኞች እንዲሆኑ ያደረጉት። ከዛም ለ25 ዓመት እርስ በርስ እየተጣላን ለህብረተሰቡ መጥፎ ምሳሌ እየሆንን አሳለፍን። ሃላፊነቱ ታድያ የኛ አይደለምን?

ሃላፊነት ወስደን ምን እናድርግ። ሁሉም በበኩሉ ማድረግ የሚችለው አለ። ሆኖም ሁሉ ስራችን መፈከር መሆን ያለበት «ክፉ አታድርግ» ነው። ይህ ማለት አብዛኞቻችን በመሃበራዊ ኑሮው ክፉ ነገር ከማድረግ ብንቆጠብ፤ ከጎረቤቶቹ ጋር ተፋቅረን ብንኖር፤ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ብንግባባ፤ ለስራተኞቻችን ደግ ብንሆን፤ የተቸገሩትን በደምብ ብንረዳ፤ ወዘተ ለውጥ ወድያው ይመጣል። ኢህአዴግም ምንም ሊከላከለው አይችልም።

ዛሬ እነዚህ አይነት አዝማሚያ እያየን ነው። በአማራ ክልል ለምሳሌ አመራሩም ፖሊሱም ወታደሩም ክፉ ነገር አላደርግም የራሴን ህዝብ አልገልም አልጎዳምም ስላለ ነው የእምቢተኝነት ንቅናቄው እዚ የደረሰው። የብአዴን አመራር ፖሊስና ወታደር በመቅጣት ብቻ ሳይሆን በተለያየ መንገድ ህዝቤን እረዳለሁ፤ በትክክል አስተዳድራለሁ፤ አልጎዳም፤ ወዘተ ካለ ኢህአዴግ ከሌሎች ክልሎች አስተዳዳሪ ፖሊስና ወታደር ወደ አማራ አምጥቶ ለመቆጣጠር ቅንጣት አቅሙ የለውም። (አለው ካልን አናሳ መሆኑን አጣን ማለት ነው!) ለጊዜው ለማስፈራራት ያህል የብዙ ሰው መግደልና ማሰር አቅም አለው እያደረገውም ነው ግን ከተወሰና ደረጃ ማለፍ አይችልም። 

ኢህአዴግም በፖለቲካ የበሰለ ስልሆነ ይህን በደምብ ይገባዋልና በዚህ ማስፈራራትና ጭቆና ነገሩን ካላበረድኩኝ መቆጣጠር አልችልም ብሎ ያምናል። በተዘዋዋሪ ዛሬም የሚካሄደው ማስፈራራት የአማራ ከሃዲዎች ባይኖሩበት ሊካሄድ አይችልም ነበር። (ከሃዲዎቹንም እኛ ነን የወለድናቸው። ቁጥራቸው በርካታ ከሆኑ በአማራ ክልል በኛ መሃል ችግር አለ ማለት ነው የከሃዲ ፋብሪካ ሆነናል ማለት ነው! ከሃዲዎቹ ላይ ከማተኮር የሚፈጠሩበትን ምክንያት አጣርቶ ማስተካከል ነው ያለብን።)

ለአማራ ህዝብ ምክሬ እንደዚህ ነው። እርስ በርሳችሁ ሰላም፤ አንድነት፤ መታማመንና ፍቅር አዳብሩ። መሃበራዊ ኑሮአችሁ ያማረ ይሁን። የቀበለ አስተዳደርን በጥሩ ሁኔታ አስፈጽሙ። ካህናት የህዝቡን የህሊና ንቃትን አዳብሩ በስብከት ሳይሆን ይበልጥ ምሳሌ በመሆን። ውስጣችሁ ያሉትን ቅራኔ ያለባቸውን ቡድኖች እንደ የተለያዩ አናሳ ጎሳዎች በጥበብና በፍቅር ያዙም የጥፋት አካል እንዳይሆኑ ተንከባከቧቸው! በማህላችሁ ያሉትን የተጎዱ ስራ ያጡ ማደርያ ያጡ ወዘተን ተንከባከቧቸው። ሰላማዊ ሁኑ፤ የሰው ቤት ማቃጠል ንብረትንም ማውደም ይቅር። ይህ የህሊናም የፖለቲካም ጉዳት ብቻ ነው የሚያመጣው። ከፍተኛ አስተዳደር ቦታ ላይ ያላችሁ በትክክል አለ ሙስና አለጥፋት አለክፋት አስተዳድሩ። ፖሊስና ወታደሮች መትፎ ነገር አታድርጉ። ሄዳችሁ እሰሩ የሚል አለአግባባ የሆነ ትዛዝ ብታገኙ እምቢ ከማለት ሰውየውን አጣን ብላችሁ ተመለሱ! ወዘተ።

እንደዚህ አይነት እርምጃዎች ሁሉም ህብረተሰብ ማድረግ ይችላል በቀላሉም መንግስትን ይለውጣል። እግዚአብሔር ከኛ ጋር ይሁን ያጠፋውንም ይቅር ይበለን ለፈተናም ካኑ ወድያ እንዳንገዛ ብርታቱ ይስጠን።

Monday, 5 September 2016

የጎሳ ብሄርተኝነትን እንዴት እንቀንስ?

2008/13/1 ዓ.ም. (2016/9/5)

በመጀመርያ እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች ስለ ጎሳ ብሄርተኝነትና የጎሳ ስሜት ወይም የማንነት (ethnic identity) ስሜት በደምብ መረዳት አለብን። የጎሳ ስሜት የተፈጥሮ ጉዳይ እንዶሆነ ማመን አለብን። የሰው ልጅ ቤተሰቡን እንደሚወድ፤ መንደሩን እንደሚወድ፤ ጎሳውን ይወዳል። አንዳንዱ ጎሳውና ሀገሩ አንድ ስለሆነ ለጎሳውና ለሀገሩ ያለው ሲሜት አንድ ነው። አንዳንዱ ደግሞ ከብዙ ጎሳ ያለበት ሀገር ስለሚኖር ጎሳውና ሀገሩን ለይቶ ለሁለቱ የተለያየ ስሜት ይኖረዋል።

የጎሳ ስሜት ተፈጥሮ እንደመሆኑ ለመረዳት አይናችንን ከኢትዮጵያ ዞር አድርገን ዓለም ዙርያ ያሉትን ሀገሮችን እንመልከት። በታዳጊም በበለጸጉም፤ በምዕራባዊም በሌላውም፤ በአዲሱም በጥንታዊውም ሀገሮች የጎሳ ስሜት ሲንጸባረቅ እናያለን። ታሪካዊ ውይም ወቅታዊ ብሶቶች ቢኖርም ባይኖርም፤ የኤኮኖሚ ጥቅም ጉዳይ ቢኖርም ባይኖርም፤ ወዘተ የጎሳና የማንነት ስሜት አለ። ከዚህ ትንታኔ በዓለም ዙሪያ ያሉትን ምሳሌዎች አልደረድርም። ግን ይህ የጎሳ ጉዳይ ዓለም ዙሪያ መገኘቱ የሰው ልጅና ማኅበራዊ ውነታ እንደሆነ ያሳያል።

ታድያ ተፈጥሮ ከሆነ ምንድንነው የጎሳ ወይም የማንነት ስሜት ችግር።? ችግሩ የሚመጣው አንድ ሰው ጎሳውን ከሀገሩ (ወይም ከመላው የሀገሩ ህዝብ) ይበልጥ ሲወድና ሲያስቀድም ነው። በመጀመሪያ ትግራይ ነኝ ቅጥሎ ኢትዮጵያዊ» አይነቱ አባባል።) ይህ ሰው ከጎሳውን መውደድና በጎሳው መኩራት አልፎ ወደ የጎሳ ብሄርተኝነት (ethnic nationalism) ተሻግሯል ማለት ነው። እንደዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ችግር እንደሆነ ለማስረዳት አንድ ምሳሌ ልስጥ፡ «የጎሳዬ ቋንቋ የአካባቢዬ የአስተዳደር፤ ትምህርት፤ ፖሊቲካ፤ ወዘተ ቋንቋ ይሁን» የሚለውን አቋም እንመልከተው። ጎሳው በአካባቢው የህዝብ ቁጥር በጣም አባዛኛ ከሆነ አቋሙ ትክክል ነው ማለት ይቻላል። ጥቂት ሰው ነው አለፍላጎቱ ይህን ቋንቋ መማር የሚኖርበት። ህዝቡ ባብዛኛው ተጠቃሚ ስለሚሆን ሀገርን የሚጎዳ አቋም አይደለም። በአንጻራዊው ደግሞ ይህ ጎሳ ከአካባቢው እጅግ አናሳ ነው እነበል። ይህ ማለት ለጥቂት ሰው ፍላጎት ተብሎ በርካታ ህዝብ በሌላው ቋንቋ በግድ ሊስተዳደር ነው። የዚህ ጎሳ ሕብረተሰብ «ምንም ይሁን ማንም ይጎዳ የኛ የጎሳ ፍላጎት ነው መቅደም ያለበት» የሚል ከሆነ ጎሳውን ከሀገሩ አስቀድመዋል። የጎሳ ብሄርተኝነት ማለት ይሄ ነው።

እንደዚህም ሆኖ የጎሳ ብሄርተኝነትን ስንቃወም መጠንቀቅ አለብን። በመጀመሪያ የጎሳ ብሄርተኛ የሆኑት ፖለቲከኞች የነሱን አቋም የሚቃዎሙትን እንደ ፖለቲካ መሳርያ በቀላሉ መጠቀም ይችላሉ። የጎሳ ብሄተኝነት ብዙ ግዜ ሆድ የባሰው ስልሆነ «የኛን አቋም የሚቃዎሙት የጎሳችን ጠላቶች ናቸው፤ መብቶቻችንንም እንዲከበር የማይፈልጉ ናቸው» ብለው በማናፈስ በቀላሉ የተከታዮቻቸውን ቁትር ይጭምራሉ። በሁልተኛ ደረጃ የጎሳ ብሄርተኛን አቋም መቀየር ከባድ ነው። ከጎሳ ብሄርተኝነት የተቀየሩ ሰዎች ጥቂትና በጣም የሚደነቁ ናቸው። እነሱም የተቀየሩት በክርክርና ብሙግት ሳይሆን ትህትና፤ ንፁህ ልብና ለዘብተኛ አቋም ያላቸው ሰዎች ስላጋጠሟቸውና እንደነዚህ አይነት ሰዎች እንደ ወንድሞቻቸው ማየት የህሊና ግዴታ ስለሆነባቸው ነው።

የጎሳ ብሄርተኝነትና ጎሳን ከሀገር ማስቀደም ምን ችግር አለው የሚሉ አሉ። የጎሳ ብሄርተኝነት ለሀገር ህዝብ ያለውን ጉዳት ባጭሩ ለማስረዳት ስለኢትዮጵያ ትንታኔ የሚሰጡ ምሁር ክሪስቶፈር ካላፓም አንድ ግዜ የጻፉትን ገላች አባባል ልጥቀስ፡ «በአንድ ሀገር የሚያራርቁና የሚያለያዩ ኃይሎች ከሚያገናኙና የሚያዋህዱ ኃይሎች ካየሉ ለሀገር ህልውና አስጊ ይሆናል» (ትርጉሙ የኔ ነው)። እያንዳንዱ ጎሳ በጎሳ ብሄርተኝነት ላይ ካቶከረ ሀገሩ ሀገር መሆኑን ቀርቶ የቅራኔ፤ ሹክሹክታና ጦርነት ስፍራ ይሆናል። ሁሉም ለራሱ ብቻ ስለሚያስብና ስለሚታገል። ለዚህ ነው የጎሳ ብሄርተኝነት ሀገርን እጅግ የሚጎዳው።

የዛረው የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥትን የመሰረተውና ላለፉት 25 ዓመታት ሀገሪቱን የመራው ኢህአዴግ ይህ የጎሳ ብሄርተኝነትን ጉዳት አልገባውም። ለነገሩ አባዛኛው የኢህአዴግ አባላት የጎሳ ብሄርተኞች ስለነበሩ አይፈረድባቸውም። (በሌላ ጽሁፍ እንደተቀስኩት የኢትዮጵያ ብሄርትኛ ነኝ የሚለው እርስ በርሱ ተፋጅቶ 1983 .. ሲደርስ የፖለቲካ ሜዳው በጎሳ ብሄርተኞች ብቻ ቁጥጥር ስር ወድቆ ነበር። ጥፋቱም መፍትሄውም ከእኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እንደሆነ አንርሳ ለማለት ነው።) «የጎሳ መብት» ብለው የሰየሙት ሃሳብ በተግባር ላይ ሲውል ሁሉ ጎሳዎች የሀገር ባለቤትነት ስለሚሰማቸው የሀገር ፍቅር ያድርባቸዋል ብለው ሰበኩ። ነገር ግን ሕገ መንግስቱም አስተዳደሩም የመንግስት መፈክሮችም ይጎሳ ብሄርተኝነት እንዲጥነክርና እንዲያከር ነው ያበረታታው! የመንግስት ድርጊቶች በሙሉ የህዝብ መለያየቱ፤ የጎሳ ውድድርና ቅራኔዎች እንዲሰፉ ነው ያደረገው። የዚህ አካሄድ ውጤት እጅግ ጎጂ መሆኑን ከኢህአዴግ ዓመራር ውስጥ ያሉም በርካታ አባላት ተገንዝበውትም መፍትሄ እየፈለጉለት ነው (ለስልጣናቸው አስጊ እንደሆነ ስለተረዱ)። ይህን ግንዛቤያቸውን የሚያሳየው ዓስር ዓመት በፊት የተጀመረው «ልማት» የሚለው መፈክር ነው። ይህ መፈክርና ቀጣይ መርህዎች የተፈጠሩበት አንድ ምክንያት የጎሳ ክፍፍል በአደገኛ ደረጃ እያየለ ስለሆነ ሀገሩን አንድ የሚያረግ ህብረ ጎሳዊ የሆነ መፈክር ያስፈልጋል ተብሎ ነው። ኤኮኖሚው ቢያድግም ልማትም ቢስፋፋም የጎሳ ብሄርተኝነቱ ጭራሽ እየሰፋ መሄዱ ለሁሉም ተመልካች ግልፅ ነውና ለዚህም ነው አንዳንድ ይኢህአዴግ ክፍሎችን ያሳሰባቸው።

የጎሳ ብሄርትኝነት በሀገራችን ምንም በዝቶ ቢሆንም መፍትሄ አለው። ዋናው መፍትሄ የሕዝባዊ «ውህደት» (integration) የሚያራምዱ መርህዎችን ማካሄድ ነው። ኢትዮጵያ እስካሁንም እንድ ሀገር ሆና ያለችው በታሪኳ የውህደት አጋጣሚዎች ነው። ጎሳዎችዋ በተለያየ መንገድ ስለተቀላቀሉ የተቀላቀለው ኃይል ሀገሪቱን አንድ አድረጎ ይዟታል። የሃማኖት፤ የመልክዓ ምድር፤ የግሳ (በፍልሰት)፤ ወዘታ ውህደቶች ናቸው ኢትዮጵያን አንድ ሀገር ያረጓትና እነዚህም ናቸው እስካሁን የጠበቋት።

ማንኛውም የመንግስት መርህ ከፖለቲካ እውነታ ጋር ካልተያያዘ አይሰራምም ጎጂም ይሆናል! ዛሬ እድሜ ለ25 ዓመታት በመንግሥት ደረጃ የጎሳ ብሄርተኝነትን መስፋፋት የኢትዮጵያ ጎሳዎች ከድሮ ይልቅ ተራርቀዋል። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል የአማርኛ ትምህርት ባብዛኛው ስለማይሰጥ ብዙ ኦሮሞ ወጣቶች አማርኛ ሳይችሉ ትምህርት ቤት ይጨርሱና ከሌላ ክልል መማርም መስራትም ያቅታቸዋል። ይህ በገዛ ሀገራቸው መወሰናቸው ደግሞ ካላቸው ይበልጥ ጎሰኝነት እንዲሰማቸው ያደርጋል። የዚህ መፍትሄ ኦሮምኛን እንደ አማርኛ የኢትዮጵያ የሀገሩ ቋንቋ ማድረግ ነው። ከዚህም አልፎ ተርፎ ሌሎች ክልሎች፤ በተለይ የጎሳ ብሄርተኝነት ጠላት የሆነው የአማራ ክልል፤ በተቻለ ቁጥር በትምህርት ደረጃ ኦሮምኛ እንዲያቀርብና ተማሪዎቹ በደምብ አድርገው እንዲማሩት ማድረግ ነው። ይህ መርህ እርግት ወጪ ይኖረዋል ግን ጥቅሙ መለካት የማይቻል ነው። ኦሮምኛ በመስፋፋቱ የሚመጣው የስነ ልቦና ለውጥና በአማራና ኦሮምያ መካከል የፍልሰት ጭማሬ ሁለት የዚህ መርህ ውጤቶች ይሆናሉ። በዚህ አካሄድ የጎሳ ብሄርተኝነት እጅግ ይቀንሳል።

ከዚህ አያይዤ ማለት የምወደው በጎሳ ብሄርተኝነት የማይታማው ጎሳ አማራ ስለሆነ ይህን ጉዳይ ለመፍታት ከሌላው ጎሳ ይበልጥ ሀላፊነት አለበት። (ላለፉት 25-45 ዓመት ለመተኛቱም መካስ አለበት!) ስለዚህም በሀገር ደረጃ ኦሮምኛ ለማስፋፋት ሁኔታዎች ባይመቹም የአማራ ክልል ብቻውን በትምህርት ቤት ደረጃ የኦሮምኛ ትምህርት እንዲካሄድ እንደ ዋና እቅድ ማድረግ አለበት። ይህ ተግባር ለምላው ሀገሪቱ ታላቅ አስተዋሶ ይኖሮዋል።

ሶስት ሌሎች ውህደትን የሚጨምሩና የጎሳ ብሄርተኝነትን የሚገድቡ መርህዎች ጠቅሼ በሌላ ጽሁፍ አብራራቸዋለሁ። እነዚህ 1) በክልሎች መካከል ፍልሰት፤ 2) እንደ ትላልቅ ከተማዎች፤ አማራ ክልል፤ ወዘተ ውህደትና የሀገር ብሄርተኝነት የሚበዛባቸው ቦታውችን ኤኮኖሚ ማዳበር ሰውው ወደነዚህ ቦታዎች እንዲ ፈልስ፡ 3) የሀገሩን የሰው ቁጥር አከፋፈል (demography) ሚዛን እንዳይዛነፍ መጠንቀቅ። ለምሳሌ የሀገር ብሄርተኝነት የሚበዛባቸው ቦታዎች እንደ አዲስ አበባ በህዝብ አለመውለድ ምክንያት የህዝብ ቁጥሩ ከሌላው ዓንጻር እንዳይቀንስ መጠንቀቅ።

በመጭረሻ ማስረገት የመፈልገው ነጥብ ያለፈው የ25 ዓመት ኢሚዛናዊ የሆነ የኢህአዴግ የጎሳ ብሄርተኝነት አካሄድ በኢትዮጵያ በርካታ ጉዳት ቢያመጣም ማስተካከል ይቻላል። ሙሉ ሀላፊነቱ ግን የኛ የሀገር ብሄርተኞች ነው።