2009/2/29 ዓ.ም.
(2016/11/8)
እንደሚታወቀው
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን
ሁለት የተወጋገዙ ሲኖዶሶች አላት፤ በኢትዮጵያ
ያለው ሲኖዶስና ስደተኛው ሲኖዶስ። ይህ ሁኔታ
የተፈጠረው ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ የቤተ
ክርስቲያናችን ፓትሪያርክ አቡነ መርቆርዮስ
በመሰደዳቸው ነው። ስለ መሰደዳቸው ሁኔታ
በዛን ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት አቶ
ታምራት ላይኔ ከመንበር እንዲወርዱ ያዘዝኩት
እኔ ነኝ ብለው እንደመሰከሩ ይታወሳል። ምንም
ቢሆን በአቡነ መርቆርዮስ መሰደድና በአቡነ
ጳውሎስ መሾም መካከል ጳጳሳቱ የመንግስት
ጫና አድሮባቸው እንደነበረ ግልጽ ነው። ሆኖም
መንግስት በቤተ ክርስቲያን ላይ ጫና ሲያደርግ
ይህ የመጀመርያ ጊዜ አልነበረም። በደርግ
ጊዜም እንዲሁ ነበር፤ በኃይለ ሥላሴም፤ ከዛም
በፊትም በነግስታቱ ዘመን የቤተ ክርስቲያን
አገልጋዮች ጳጳሳቶችዋ ይህ ፈተና ሁልጊዜ
ዪደርስባቸው ነበር። ሆኖም የዛሬው ክፍፍል
ምንጭ ይሄው የመንግስት ጫና በሲኖዶሱ ላይ
በመሆኑ ነው።
ታድያ
መፍትሄው ምንድነው?
እንደሚታወሰው
በሲኖዶሶቹ መካከል እርቅ ለማምጣት በተለያየ
ጊዜ ግለሰቦችም፤ ሽማግሌዎችም፤ እንዲሁም
የቤተ ክርስቲያን ሃላፊዎች ሞክረዋል።
አንዳንዱም ሙከራ ጥሩና ያልተጠበቀ የማቀራረብ
ውጤቶችን አሳይተዋል። ግን እስካሁን ጉዳዩ
አልተቋጨም።
በዚህ
ጽሁፍ የጉዳዩን ጠቅላላ ይዞታ አልተችም፤
ጉዳዩና የእርቅ ስራው እጅግ ከባድና ውስብስብ
ናቸውና። በዚህ ጽሁፍ ከጉዳዩ አንዱን ንብርብር
ለመላጥ ነው የምሞክረው፤ ይህ ደግሞ ሲኖዶስ
ሊሰደድ ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው።
ይህን
ጉዳይ ለዘብ ባለ መንገድ ከታየ ስምምነት ላይ
እንደሚደረስና ችግሩም መፍትሄ አንደሚያገኝ
እርግጠኛ ነኝ። ነገር ግን አክራሪ አስተያየቶች
ናቸው የሰፈኑት። እነዚህ «ሲኖዶስ
ሊሰደድ አይችልም»
እና
«መንግስት
ሲኖዶስ ላይ ጫና ካደረገ ፓትሪያርኩ ግድ
መሰደድ አለባቸው ስለዚህ ሲኖዶሱ ውጭ ይሆናል
ማለት ነው»
የሚሉት
ናቸው።
በመጀመሪያ
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በማንም የኦርቶዶክስ
ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ሲኖዶስ መንቀሳቀስ
አይችልም የሚል ህግ የለም፤ ሊኖርም አይችልም።
ጣልያን ኢትዮጵያን ወርራ ከአንድ በስተቀር
ጳጳሳቱን በሙሉ ረሽና ቢሆን እኚህ አንድ
የቀሩት ጳጳስ ተሰደው ቤተ ክርስቲያኑን ካሉበት
ቢመሩ ህገ ወጥ ነው?
በፍጹም።
ግን ዋናው ጥያቄ ህገ ወጥ ነው ወይ ሳይሆን
ክርስቲያናዊ አይደለም ወይ?
ቤተ
ክርስቲያን በዚህ መንገድ እራስዋን ማዳንና
በጎቿን መጠበቅ አለባት። አንዳንድ ሁኔታ
መሰደድን ያስገድዳልም ይመክራልም።
እነዚህ
ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ አስቀድሞ አይታወቅም፤
ጊዜው ሲደርስ ሁኔታው ተጠንቶ ነው መወሰን
የሚቻለው። ለዚህም ነው ከላይ ስለ ሲኖዶስ
መሰደድ ቤተ ክርስቲያናዊ ህግ ሊኖር አይችልም
ያልኩት። እንደ ሁኔታው፣ እንደ አደገኛነቱና
እንደ አስፈላጊነቱ ውሳኔው ይለያያል።
ለዚህ
እውነታ ጥሩ ምሳሌው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ
በ1910
በሩሲያ
ኮምዩኒስት አብዮት ምክንያት መሰደዱ ነው።
የሶቪዬት ኮምዩኒስት መንግስት በቤተ ክርስቲያንዋ
ላይ ያደረሰው ጥቃት እጅግ ከባድ በመሆኑ
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ካህናትና አማኞች
በህሊናም ቢሆን ለማሰብ ያስቸግራል። በመቶ
ሺዎች የሚቆጠር ያህል ካህናት ናቸው በተለያየ
መንገድ የተገደሉት። ሌሎቹ በሞት እስር ቤቶች
ታሰሩና አብዛኞቻቸው ሞቱ።
በዚህ
ሁኔታ በ1913
የሩሲያ
ኦርቶዶክስ ፓትሪያርክ ቅዱስ ቲኾን ቤተ
ክርስቲያንዋ ታላቅ ችግር ላይ መሆንዋንና
የሶቪዬት መንግስት ካህናት እየገደሉ የራሱን
ካድሬዎች ካህን አድርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያን
እያስገባ እንደሆነ ተገንዝበው በውጭ ያሉት
የተሰደዱት ጳጳሳት እራሳቸውን እንዲያስተዳደሩ
አዘዙ። ያሉበትን ሁኔታም ለመገምገምና ይህ
ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሶስት አመት ፈጀባቸው።
ሲኖዶሱ፣ ማለትም ጳጳሳቱ በመንግስት ቁጥጥር
ስር እንደሆኑ ሲያውቁ ነው ፓትሪያርኩ ውጭ
ላሉት ጳጳሳት ካሁን ወዲያ በኛ መተማመን
አትችሉምና እራችሁን ቻሉ ያሏዋቸው።
ሆኖም
የውጩ ፓትሪያርክ ወዲያው አልተሾመም።
ፓትሪያርክ ቲኾን ከተሰዉ (አሁን
ቅዱስ ቲኾን ናቸው)
በኋላና
የሩሲያ (ሞስኮብ)
ሀገረ
ስብከት ከመጠን በላይ የካድሬ ግዛት ሲሆን
የውጭ ሲኖዶሱ ፓትሪያርክ ሾመ። ከዛ ቀጥሎ
እስከ 1999
የሩሲያ
የውጭ ሲኖዶስ (ROCOR)
እና
የሞስኮብ ሲኖዶስ ተለያይተው እንዲሁም ሲወጋገዙ
ቆዩ።
በ1999
ሁለቱ
ሲኖዶሶች ተታረቁ። የውጭ ሲኖዶሱ ከማን ጋር
ነው የትታረቀው፤ የሩሲያው ሲኖዶስ በካድሬ
የሞላ አልነበረምን ብላችሁ እያሰባችሁ ይሆናል።
በሚገርም ሁኔታ ካድሬ ያልሆኑ ታላላቅ
አባቶችና መነኮሳት አንገታቸውን ደፍተው
ከፖለቲካ ራሳቸውን አርቀው እየታሰሩ
እየተፈቱ እየተደበቁ የሶቪዬት ኮምዩኒስት
ዘመንን ያሳለፉ
ነበሩ።
አንዳንዶቹ ጭራሽ ራሳቸውን እንደ ካድሬ
አስመስለው ሌሎች ወንድሞቻቸው ካህናትን
ክጥቃት የመጠበቅ ስራ ይዘው ነበር። አሁንም
በሀገራችን በኢትዮጵያ
ከጳጳሳቱና ሀገረ ስብከቱ የካድሬ መንፈስ፤
የካድሬ ብቻ ሳይሆን ሲብስ የተራ ሙስናና
ሐጥያት መንፈስ፤
ቢኖርም ከዛ መካከል እጅግ ብፁ የሆኑ አገልጋዮች
እንዳሉ እናውቃለን። ካድሬ የሚባሉት ውስጥም
እንደሁላችንም ከራሳቸው ጋር እየተሟገቱ
ንስሀ እየገቡ እየወደቁ
እየተነሱ የሚኖሩ አሉ። በሩሲያም ሲኖዶስ
እንዲሁ ስለነበር
ነው እርቅ ላይ
ሊደርሱ የቻሉት።
በተዘዋዋሪ
በዚህ በሩሲያ ታሪክ ሌላ አስደናቂ ሁኔታ
ተፈጥሮ ነበር። በሁለተኛ የአለም ጦርነት
ጀርመኖቹ ለተወሰነ ጊዜ ምእራብ የሶቪዬት
ህብረትን ተቆጣጥረው የሩሲያ ኦርቶዶክስ
ሀገረ ስብከት የተዘጉትን በሺህ የሚቆጠሩ
ቤተ ክርስቲያኖችን እንደገና እንዲከፍት
ፈቀዱ። ከግድያ የተረፉት እውነተኛ የሆኑት
ካህናት ይህን ነፃነት ተጠቅመን ህዝቡን
እናገልግል ወይስ የሀገራችን ወራሪ የሰጠንን
ነፃነት ለክርስቶስም ቢሆን ልንጠቀምበት
አይገባም በሚለው ጥያቄ ልባቸው ተከፋፍሎ
ነበር። ምእመናኑ ሃይማኖቱ እጅግ ጠምቷቸው
ስለነበር በርካታ ካህናት ወደ ቤተ ክርስቲያኖቻቸው
ተመልሰው አገለገሉ። ጦርነቱ ሲይበቃም የሶቬት
መንግስት እንደዚህ አይነት ካህናትን እንደጠበቁት
እስር ቤት ላካቸው ወይም ረሸናቸው። (ስለዚህ
ታሪክ «ካህኑ»
የሚባለውን
የሩሲያ ፊልም እንድታዩ እጋብዛችኋለው፤
እጅግ አስተማሪ ነው።)
የሩሲያ
ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመሰደድ ታሪክ
የሚያሳየን የሲኖዶስ መሰደድ ጉዳይ እንደ
በርካታ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጉዳዮች
«ጥቁርና
ነጭ»
አይደለም።
እንዲህ ቢሆን ይሰደዳል እንዲህ ቢሆን አይሰደድም
የሚል አስቀድሞ ሁሉንም ሁኔታ የሚያካትት
ህግ የለም። እንደ ሁኔታው ነው ውሳኔ የሚወሰነው።
ታድያ
በኢትዮጵያ በ1983
የነበረው
ሁኔታ አቡነ መርቆርዮስ የሲኖዶስ መንበራቸውን
ይዘው እንዲሰደዱ ያስገድዳቸው ነበር?
ይህ
ጥያቄ እውነት ወይ ውሸት የለውም፤ እንደ
እያንዳንዱ ሰው አመለካከት ነው። አዎን
መንግስት በጳጳሳቱ ላይ ጫና እያደረገ ነው
ግን ያን ያህል ስላልሆነ መሰደድ አያስገድድም፤
ጳጳሳቱ ጫናውን ሊቋቋሙ ይገባል ማለት ይቻላል።
ወይም ጫናው የቤተ ክርስቲያኑን መሰረት
አናግቶታልና በነፃነት ምእመናኑን ለማገልገል
ሲኖዶሱ ከሀገር ውጭ መሆን ነበረበት ማለት
ይቻላል። ሁለቱም አስተያየቶች ያስኬዳሉ።
ከዚህ
መማር የምንችለው ታላቅ ትምህርት ሁሉም ነገር
እንደ ሃይማኖት ዶግማ ወይም ቀኖና ማየት
የለብንም። በነዚህ ታሪኮች አንድ እውነት
ብቻ ነው ያለው። ስለሆነም እነዚህን የመሰሉ
ችግሮችን እንደ ዶግማ እና ቀኖና እንደ
አስፈላጊነቱ የማይሻሻሉ አድርገን ማየት
የለብንም። ከሃይማኖታችን መሰረተ ትምህርትና
ስርዓት በቀር ሌላውን ጉዳይ በሙሉ በትህትና
ነው ማየት ያለብን። አቋሞቻችንንም በትህትና
መያዝና ሃሳቦቻችንን መቀየር መቻል አለብን።
ጥሩ ክርስቲያን አንድ አምላክ እግዚአብሔርን
እንጂ ሃሳቡን፣ የሚከተለውን ርዕዮት አለም፤
ወይንም አቋሙን አያመልክም።
በመጨረሻ
አንደ
ልጠቅስ
የምፈልገው ነገር
አለ፤ ሁለቱ
ሲኖዶሶቹ
ቢታረቁ
ለሀገራዊ እርቅ ሰላምና የመንፈሳዊ ደስታና
መረጋጋት ታላቅ ድል ይሆናል። በዛሬው
ኢትዮጵያ ህዝቡ ያጣው መሪ
ነው የሚባለው እውነት ነው። ልጄ ሲያድግ እንደ
ከሌ ቢሆንልኝ የሚባል መሪ በየትኛውም በመንግስትም
በሃይማኖትም በመሃበራዊም ዘርፍ የለም።
ከግዥ መደቡ ጥሩ ምሳሌ የሚባልና
የሚደነቅ የለም፤
ጭራሽ
ህዝቡ ሙስናና ተመሳሳይ መትፎ ስነ መግባር
ውስጥ ሲገባ መሪዎቻችንም ያደረጉታልና
ለምን እኛም
አናደርገውም እያለ
ነው። ስለዚህ እንደ ሲኖዶስ እርቅ አይነቱ
ዜና
ከቤተ
ክርስቲያን መሪዎች ቢመጣ
ለህዝባችን ታላቅ ምሳሌና
ለሀገራዊ እርቅ ታላቅ ድል ነው የሚሆነው።
ይህ
እርቅን
ለማምጣት ደግሞ በሃይማኖታዊም
በፖለቲካውም አቅጣጫ ቢታይ ከባድ ያልሆነ
ጥቅሙ ከጉዳቱ እጅግ ከፍ ያለ ነግር
ነው።
ከሌሎች ጉዳዮች ይልቅ
ብዙም ከባድ አይደለም።
እግዚአብሔር
ይህንን እርቅ
ለማድረስ
ልቦናውን ይስጠን።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!