Friday, 18 January 2019

Unraveling NAMA's "Intellectual Cover"

የአማራ ብሄርተኝነት በመሰረቱ የብሶት ፖለቲካ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/07/blog-post_30.html) ነው። የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) መሪዎችም ተከታዮችም በትርክታቸው የሚያተኩሩት ስለአማራ ላይ የደረሰው የ27/44 ዓመት በደል ነው። አማራ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ተለይቶ ተበድሏል ይላሉ። አልፎ ተርፎ ካሳም ይገባዋል ይላሉ። ከፖለቲካዊ ፕሮፓጋንዳዎቻቸው ምናልባት 80%ኡ ስለዚህ ስለ አማራው መጨቆን ነው። ይህ የአማራ ብሄርተኝነት በመሰረቱ በብሶት የሚመራ ንቅናቄ መሆኑን ያስረዳል።

ሆኖም እንደ ማንኛውም ፖለቲካ ንቅናቄ የአማራ ብሄርተኝነት ትርክት እና ፖለቲካዊ ጽንሰ ሃሳብ (theory) ያስፈልገዋል። ይህ intellectual cover (የምሁራን ሽፋን ልበለው?) የአብን ምሁራኖች በደምብ ሰርተውበታል። ዋናው የዚህ ሽፋን መልእክት እንዲህ ነው፤

«የአማራ ብሄርተኝነት የሚያስፈልገው የሌሎች (ያጠቁን) የጎሳ ብሄርተኝነቶችን በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዳያመዝኑ ማድረግ ነው። የአማራ ብሄርተኝነት የሌሎች የጎሳ ብሄርተኝነቶችን balance በማድረግ የአማራንም የኢትዮጵያንም ህልውና ይጠብቃል።»

ማንኛውም ትንሽም ስለፖለቲካ/ታሪክ የሚያውቅ ሰው ይህ ትክርት እጅግ የተሳሳተ እንደሆነ ያውቃል። በርካታ ጎሳዎች ወይንም ክልሎች ባሉባቸው ሀገራት የስልጣን ውድድር በመሃል እና በክልሎቹ እንደሆነ የታወቀ ነው (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/10/on-nama-strategies.html)። ስልጣን ከምሃሉ (ኢትዮጵያዊነት) ወደ ልልሎች (ጎሳ ብሄርተኝነት) ቁጥር ሁሉም ጎሳ ብሄርተኞች ይጠነክራሉ። የጎሳ ብሄርተኞቹ ከእርስ በርስ ይልቅል የሚሟገቱት ከመሃሉ (ከኢትዮጵያዊነት) ነው። ዋናው አላማቸው መሃሉ ማድከም ነው። በዚህ ጋራ አላማቸው ይተባበራሉ። መሃሉ መንምኖ ሲያበቃው ስልጣን በሙሉ በጎሳ ብሄርተኞች እጅ ይሆናል። ከዛ እነዚህ የጎሳ ብሄርተኞች (ለምሳሌ ህወሓት፤ ኦነግ፤ አብን፤ ወዘተ)እርስ በርስ መደራደር አይችሉም። በጎሳ እና ብሶት የተመሰረቱ ስለሆነ የጋራ ማንነት እና ጥቅም ስለማይታያቸው የሚደራደሩት በባዶ ድምር (zero sum) አቋም ነው። ወጤቱ ጦርነት እና መለያየት ነው የሚሆነው። ሰለባው በየክልሉ የሚኖር አማራ፤ አማራ ክልል፤ መላው ኢትዮጵያዊ ነው የሚሆነው። መሃሉ ሲመነምን እና ጎሳ ብሄርተኞች ሲጠነክሩ ውጤቱ ይህ ነው።

እስቲ በዚህ ረገድ አንዳንድ የአብን አስተሳሰብ የውስጥ ተቃርኖዎች (inconsistencies) እንመልከት። በአንድ በኩል የጎሳ አስተዳደርን (ethnic nationalism) እንቃወማለን፤ የዜጋ ፖለቲካ ነው የሚያስፈልገው ያላሉ። በጎሳ የተደራጀነው ነባራዊው ሁኔታ አስገድዶን ነው እንጂ የጎሳ አስተዳደር ይቁም ይላሉ። የጎሳ አስተዳደር መኖር የለብትም ሲሉ ደግሞ ምክንያቱ አንድ ሀገር በጎሳ ሲስተዳደር ግጭቶች ይበዛሉ ነው። ኦሮሚያ የሚኖሩ አማሮች ይጠቃሉ፤ ነባር እና መጤ ግጭት። ጠረፍ ላይ ግጭት ይኖራል፤ የመሬት ግጭት። በሁሉም የፖለቲካም የማህበረሰብም መስክ ሰው ጎሳውን አስቀድሞ ኢ-ፍትሃዊነት ያራምዳል፤ የፍትህ ግጭት። ለዚህ ነው የጎሳ አስተዳደር የግጭት ምንጭ ነው እና ይቅር የሚባለው። በሌላ አባባል ፖለቲካ በጎሳ ብሄርተኝነት ሲመራ ግጭት ይመጣል ነው። እንዲህ ከሆነ ኢንዴት ነው አብን እንደሚለው የአማራ፤ የኦሮሞ፤ የትግራይ ወዘተ ብሄርተኞች ኢትዮጵያዊነትን አፍርሶ እንደገና በድርድር መገንባት የሚችሉት! የጎሳ ብሄርተኞች መደራደር አይችሉም ተብሏል። አሁን ደግሞ መደራደር ይችላሉ። ሃሳቦቹ ይቃረናሉ።

አልፎ ተርፎ «የኢትዮጵያ የብሄር (ጎሳ) እስር ቤት ናት፤ ሰለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጎሳው ይሰብሰብ እና እነዚህ የጎሳ ብሄርተኛ ስብስቦች አንዲስ ኢትዮጵያ ይመስርቱ» የሚለው ሃሳብ በ1950/60ዎቹ በማርክሲስት የተማሪ ንቅናቄው የተወለደ ነው። እስከ ዛሬም እነ ህወሓት፤ ኦነግ እና ሌሎች ጎሳ ብሄርተኞች ይህንን አቋም ነው የያዙት። በ1983 ህወሓት ስልጣን ሲይስዝም ይህን ነው አሰምሮ የተናገረው። «እንዳንተ «አንድነቶች» ኣናንተ «አማሮች»፤ እምዬ ኢትዮጵያ ከማለት በጎሳችሁ ተሰብሰቡ እና ተደራደሩ» እያሉ መሃይም ጥሩምባቸውን ይነፉ ነበር። ይህ ሃሳብ ወድቅ መሆኑ የገባን ደግሞ የጎሳ ብሄርተኞች ስብስብ ጦርነት እንጂ ሰላም አያመጣም ነበር። እንሆ ውጤቱን አየነው። ፖለቲካ በጎሳ ሲሆን ጸብ ብቻ ነው የሚኖረው። የጎሳ ፖለቲካ በተፈጥሮ የዜሮ ድምር አስተሳሰብን ይከተላልና።

ስለዚህ አብን ይህንን ታሪክ አውቆ እንዴት ነው ወደ ጎሳ ፖለቲካ እንመለስ የሚለው? አይገባኝም። እኔ እንደሚመስለኝ የሚገባ ብሶት እና ቅሬታቸውን የምሁራን ልብስ (intellectual cover) ለማልበስ ብለው የአብን ልሂቃን እራሳቸውን ወደ የማይሆን ትምዝምዝ ውስጥ አስገበተዋል። የአማራ ብሄርተኝነት በዚህ መልኩ ምንም አይነት ምሁራዊ ድጋፍ የለውም እና ሊፈጥሩ ለት አይችሉም። የብሶት የጎሳ ብሄርተኝነት ነው፤ ሌላ ነገር አንፍጠርለት። አንዴ ይህንን ካመንን በኋላ እንዴት ነው የህዝቡን ብሶት እና በደል በሚጠቅመው ሁኔታ ማስተናገድ የሚቻለውን የፖለቲካ ጥያቄን ለመመለስ እንስራ።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!