Wednesday, 16 January 2019

የድሮ ስረአት ናፋቂ ነኝ!

የአብን አመራሮች ክርስቲያን ታደለ እና በለጠ ሞላ እራሳቸውን «ትምክሕተኞች» ነን ካሉ እኔም እውነቱን ለመናገር በአቅሚቲዬ «የድሮ ስረአት ናፋቂ» ነኝ ማለት የምችል ይመስለኛል። የኃይለ ሥላሴ መንግስት ከስልጣን ሲወድቅ እድሜዬ ገና ሁለት ዓመት ቢሆንም ታሪክ በመስማት ስሜቴ ያንን ዘመን እንድናፍቀው አድርጎኛል።

ግን ዘመኑም አገዛዙም በርካታ ችግሮች ነበራቸው። የፍትህ እጦት፤ አድሎአዊነት፤ ወዘተ ነበረ። ሁላችንም እንደምናውቀው በርካታ ጪሰኞች እነሱ ወይንም አባት አያቶቻቸው ከመሬታቸው ተፈናቅለው በኢፍትሃዊ አሰራር ባላባቶችን ያገለግሉ ነበር። እንደዚህ አይነት ችግሮች እንደነበሩ እያወኩኝ እንዴት ያዘመን ይበልጥ ያስረአት ይናፍቀኛል።

ለቤተሰቦቼ ያዘመንን ጥሩ ነበር። ችግሩ እነሱን በቀጥታ አላጠቃም እና እነሱ በሰላም እና ብልጽግና ይኖሩ ነበር። ደርግ ሲመጣ ግን ችግር እየመጣ ጀመረ። የፖለቲካ ቀሱም ቤታችን ላይ ሊያንኳኳ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደርግን ጠላሁ የጃንሆይ መንግስትን ናፈኩኝ። እንደ ማንኛውም ልጅ የራሴ ህይወት እና ልምድ (experience) አመለካከቴን ወሰነው።

መቼም አሁን ይህ አመለካከት የተሟላ እንዳልሆነ ይገባኛል። እኔ እና ቤተሰቦቼ ሰላም ስለነበራቸው ያዘመን እና ስረአት ጥሩ ነበር ማለት እንዳልሆነ ይገባኛል! ግን አሁንም ይናፍቀኛል። ለምን? ያኔ እኛ ኢትዮጵያዊያን የቆፈርነው ጉድጓድ ገና ብዙ ጥልቅ አልነበረም! ማለትም በርካታ ችግሮቻችንን በቀላሉ በአንዳንድ ትናንሽ ማስተካከያዎች ልናስወግድ እንችል ነበር። የኔ መሬት በሽ ነበር፤ ደን ነበር፤ ልሂቃኖቻችን ብዙ በማርክሲዝም አልተዋጡም ነበር፤ ጎሰኝነት አልሰፈነም ነበር። ተስፋ ቅርብ ነበር።

አሁን ግን ተጨማሪ ሌላ የ50 ዓመት የጉድጓድ ቁፈራ አካሄደናል። ጥልቅ የሆነ ጉድጓድ ውስጥ ነን። አሁንም ተግተን ሰርተን መውጣት እንችላለን ግን ስራው ከበፊቱ ይልቅ እጅግ ከባድ ነው። ብዙ በጣም የተመላሹ ነገሮች አሉ።

ስለዚህ አዎን የድሮ ስረአት ናፋቂ ነኝ። ግን የምናፍቀው ምክንያት ያኔ ችግሮች ቢኖሩም እንደ ዛሬ ያህል ለማስተካከል አይከብዱም ነበር ብዬ ስለማምን ነው። እንጂ የጃንሆይ ዘመን እና ስረአት ችግሮች አልነበረባቸውም ለማለት አይደለም!

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!