Thursday, 3 January 2019

አንዳንድ ሃሳቦች፤ የአንድነት አና የአማራ ብሄርተኝነት ፖለቲካ

ከአብርሃም ጮራ ገንቢ ጽሁፍ (https://www.facebook.com/abrham.tibebu/posts/10155875239026471) ተከትሎ አንዳንድ ሃሳቦች፤

1. የአንድነት አቋም እና ድርጅት/ደጋፊ/ሰው እንለይ። አቋም እና ሰው እንለይ። እንደማንኛውም ፍሬያማ ውይይት ሃሳብ እና ሰውን መለየት ያስፈልጋል። ይህ ባለመሆኑ አንዳንድ ሰዎች እንደ ግንቦት 7 አይነቱን የማይወዱትን የ«አንድነት ኃይል» ለመኮነን የአንድነት ጽንሰ ሃሳቡንም ይኮንናሉ። እንደሚገባኝ አብን (ለምሳሌ) ሁለት ግብ ነው ያለው፤ 1) የአማራ ህዝብ መብትን ለማስከበር 2) ኢትዮጵያ ዙርያ የጎሳ አስተዳደር የንዲፈርስ እና የዜግነት ፖለቲካ እንዲሰፍን። ስለዚህ አብን በ«አንድነት» ያምናል። ግን አንዳንድ የአብን ደጋፊዎች ግንቦት 7ን ወይንም ሌሎች የማይወዱትን ለመኮነን እራሳቸው የሚያምኑበት የአንድነት ወይንም የዜግነት ፖልቲካን ይኮንናሉ!

2. ሃላፊነት እንውስድ፤ ሁላችንም የአማራ ብሄርተኞችም (ሁሉ አይነት የአማራ ብሄርተኞች) የተወሰነ ዓመታት በፊት የአንድነት ኃይሉ አካል ነበርን። ለምሳሌ የቅንጅት ደጋፊ ነበርን። ወይንም የመኢአድ ደጋፊ፤ ወይንም እድሜአችን ጠና ከሆነ የኢዲዩ ደጋፊ። ወዘተ። ስለዚህ የአንድነት አስተሳሰብንም የአንድነት ድርጅቶችንም እንደ ባይተዋር አንመልከታቸው። እራሳችን ከነሱ ነበርን/ነን።

3. የምዕራባዊያን/ማርክሲስት/ወዘተ ጨቋኝ ተጨቁኝ ውየንን us vs them ሃሰተኛ ትርክት እናቁም! አሁን ያለው የሃሳብ ግጭት ነው። ለምሳሌ፤ የ«አንድነት ኃይሉም» «አማራ ብሄርተኛውም» በአንድነት/ዜግነት ፖለቲካ ያምናል። ያሁኑ ህገ መንግስት ፈርሶ ጎሳ/ዘር የሌለበት ሀገ መንግስት መኖር አለበት ያልሉ ሁለቱም አንድነቶቹም አማራ ብሄርተኞችም። ታድያ ልዩነቱ ምንድነው? የስልት (strategy) ምናልባትም የታክቲክ ነው። አንድ አቋም እያለን በአካሄድ ከሆነ ልዩነታችን መቦጫጨቁ ሁለታችንንም እንደሚጎዳ ግልጽ ነው። ታሪክ መድገም ነው የሚሆነው።

4. ልጅ የሆኑት የአማራ ብሄርተኞች እኛ የ60ዎቹ ተቃራኒ ነን ይላሉ። ግን ይህ us vs them dialectical ትርክት የ60ዎቹ መሰረታዊ አካዬድ ነው!! ከሃሳብ ይልቅ ሰው/ቡደን ላይ ማተኮር ይ60ዎቹ አካሄድ ነው። በስልታዊ ልዩነት መፋጀት የ60ዎቹ «ሌጋሲ» ነው። ፌው ከዛፉ ርቆ አይወድቅም። የአባቶቻን ስህተት አንድገም። የ60ዎቹ የ«ጠላት/ወዳጅ» ፖለቲካ የተጠቀሙት በቀላሉ ተከታዮች በስሜት ለማሰባሰብ ነው፤ እንደ ህወሓት ማለት ነው። ለዚህ ግብ ይህ ጠላት/ወዳጅ ትርክት ማንዴላ እንዳለው ጥይት/መድፍ ነው። ስልጣን ያመጣል ግን ሀገር ያፈርሳል።

5. Counterforce ጥሩ ይመስላል ግን አይሰራም። ነገ አማራ ተደራጅቶ ከነ ህወሓት እጥፍ ድርብ ጠንካራ ሆነ hard እና soft powerኡን በገንዘብ፤ በinfluence፤ በኔትዎርክ ወዘተ ሌሎች ክልሎች ላይ ጫና መፍጠር ይችላል ነው የcounterforce ሃሳብ። ይህን ለማድረግ መሃሉን መያዝ (capture the centre) አለበት ልክ ህወሓት እንዳደረገው። በዛሬ ነባራዊ ሁኔታ አማራም ሌላም የጎሳ ብሄርተኝነት ይህን ማድረግ እንደማይችል መቼም ለሁሉም ግልጽ ይሆናል ብሄ እገምታለሁ። ሌሎች ጎሳዎች ምንም ያህል ከአማራው ደካማ ቢሆኑም ይህን አይፈቅዱም። ሁከት እና ሽብር ይሻላቸዋል። አማራው ይበልጥ ለአማራ ብቻ በቆመ ቁጥር እነሱም ወደ ራሳቸው ይሸገሸጋሉ። ጠንካራ የአማራ ብሄርተኝነት የአማራ ክልልን ልዋላዊነት ያስከብራል ብዬ አምናለሁ። ግን ከሌሎች ጎሳ ድርጅቶች ጋር መስማማት አይችልም።

6. ህወሓት ከሌሎች ጎሳዎች ጋር መተባበር የቻለው ለምን አማራ ብሄርተኛው አይችልም ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ህወሓት መቼ ቻለ! ለጊዜው (27 ዓመት) አማራን ጥላት በማድረግ ጎሰኝነትን በማስፈን ከጎሰኞች ጋር ህብረት ፈጠረ። በሌላው በኩል ጸንፈኛ ጎሰኞች እንዳይመጡብህ እጠብቅሃለው ብሎ ሌላውን በፍርሃት ያዜ። ግን ሁሉም አሻጥር የማይሆን ከጥላቻ ወይንም ከአሉታዊነት ውጭ የሌላው መሰረት ነበር። ዛሬ ጠንካራ አማራ ብሄርተኛው ይህን ላድርግ ቢል ማን እንደሚተባበረው አይታየኝም።

7. በአጭሩ ጠንካራ አብን (የዛሬው ሳይሆን እንደሚፈልገው ስራውን ሰርቶ የጠነከረ እና የአማራ ክልል ሙሉ ድጋፍ ያለው) ከሌሎች የጎሳ ድርጅቶች ጋር መወየየት አይችልም። የጎሳ ስብስብ ተወያይቶ መስማማት አይችልም። ሁልጊዜ ወደ ግጭት ያመራል። ምርጫው ሀገሪቷን መከፋፈል ነው የሚሆነው። ይህም በብዙ ደም ነው የሚካሄደው ብየቦታው minorityዎች ወደ «ቦታቸው» መመለስ ስለሚኖርባቸው።

8. በህብረ ጎሳዊ ሀገር force/counterforce በጎሳዎች መካከል ቀውስን ነው የሚያመጣው። ስንሰ ሃሳቡን ትተን empirically በኢትዮጵያም አይተነዋል እያየነው ነው። በህበረ ጎሳዊ ሀገር ታላቁ force/counterforce በመሃሉ እና በጎሳዎቹ መካከል ያለው ነው። መሃሉ በጠነከረ ቁጥር ሰላም እየሰፈነ ይመጣል ጎሳዎችን አለፍላጎታቸው ካልጨፈለቀ ድርስ። ጎሳዎቹ እየጠነከሩ መሃሉ በላላ ቅጥር ጎሳዎቹ እርስ በርስ ያላቸው ልዩነት እየከረረ ይሄዳል ማለት ነው። ልዩነታቸው ጨመረ አንድነታቸው ቀነሰ። ይህ የግጭት መንስኤ ነው። አንዱ ጎሳ ከሌላው ምንም ያህል ቢጠነክር በኃይል ይሁን በድርድር ሰላምን ሊያመጣ አይችልም።

9. ስለዚህ አብን ለሌሎች ጎሰኞች counterforce መሆን ለግቤ ይጠቅማል ብሎ ማሰብ የለበትም። ለኔ ዋናው የአብን ስትራቴጂካል ጥቅም (ሌሎች ቢኖሩም) የአማራ ክልልን ከህወሓት ናፋቂዎች፤ ክሙስና፤ ከሞራል ዝቅተት ወዘተ ለማዳን መስራት ነው። ያለውን የአማራ ብሄርተኝነት ስሜትን ወደዚህ አይነት አውንታዊ አቅጣጫ ማሰማራት ነው። አማራ ክልልን rehabilitate ማድረግ ነው።

10. እንጂ አብን የአማራ ብሄርተኝነትን አስፋፍቼ የአንድነት ፖለቲካን አጥፍቼ እንደገነ ገነባለሁ ከሆነ ለአማራ ህዝብም ለሁሉም ቀውስ ነው የሚያመጣው።

11. የአማራ ብሄርተኝነትን እንደ መሳርያ ተጠቅሜ በኋላ ተወዋለሁ ማለትም አይቻልም! አንዴ የፖለቲካ ውጤት ካመጣ ማንም ፖለቲከኛ አይተወውም። «ሱስ ይሆናል»! ይህ መቼም የታወቀ የፖለቲካ ሃቅ ነው።

12. የአንድነት ፖለቲካ መሰረታዊ ችግሩ የመጠላለፍ ፖለቲካ (https://asfawdarguemeshal.blogspot.com/2018/09/blog-post_21.html) ነበር አሁንም ነው። በጃንሆይ ዘመንም መንግስታቸው ውስጥ የነበረው የእርስ በርስ ሹኩቻ ነው መንግስታቸውን አድክሞ ለውጦች አንዳያደርግ እና እንዲፈርስ ያደረገው። የተማሪ ንቅናቄውንም የፈጠረው። ከዛ ኢዲዩ፤ መድህን፤ ግራኞቹ (ኢህአፓ፤ መኢሶን፤ ወዘተ)፤ መኢአድ፤ ቅንጅት ወዘተ ቁም ነገር ላይ መድረስ ያልቻሉት በመጠላለፍ ፖለቲካ ባህል ምክንያት ነው በመሰረቱ። ይህ ችግር ግን የአንድነት ወይንም የዜግነት ፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ሳይሆን የፖለቲካ ባህል ችግር ነው።

13. በሁለተኛ ደረጃ ነው የነ ቅንጅት ችግር የ«ነፍጠኛ ነህ» ክስ። ይህን ክስ ለማስቆም እና ከራሱ የጎሳ መጨፍለቅ ሃሳብ ለማውጣት ብሎ ነው የአንድነት ፖለቲካው አማራ ያልሆኑትን በተጨማሪ ማቀፍ የፈለገው። ለመድገም ያህል ሁለት ምክንያት፤ 1) አማራ ብቻ ነህ እናይባል እና 2) ኢትዮጵያ multicultural መሆን የለባትም የሚሉትን ከማህሉ ለማውጣት። ግን ይህን በማድረግ፤ ለምሳሌ መድረክን በመፍጠር፤ የአንድነት ኃይሉ የተወሰን መሻሻል ቢያሳይም መጠንከር አልቻለም። ለምን፤ ከላይ ያልኩት መሰረታዊው የመጠላለፍ ፖለቲካ ባህል ስላለቀቀው። ያበደምብ address አልተደረገም።

14. ታድያ ለምንድነው እነ አብን፤ ህወሓት እና ሌሎች የጎሳ ፓርቲዎች ይህ የመጠላለፍ ፖለቲካ ባህል የማያጠቃቸው? ያው ጎሰኝነት ስሜታዊ አንድነት ስለሚያመጣ ትብብርን ይጨምራል፤ የታወቀ ነገር ነው። የጎሰኝነትን ግን ትክክለኛ ጽንሰ ሃሳብ አያደርገውም!! የጎሳ ፖለቲካ ድርጅት በ mobilization ዋና ቢሆንም ለጭኮና እና ግጭትም ዋና ነው። ህወሓት መጀመርያ የማይስማሙትን ትግሬዎች አጠፋ። በኃይለ ጎሳ ትግራይን ተቆጣጠረ ጠላት አለህ ብሎ እይሰበከ። ስለዚህ ጎሰኝነት ለፖለቲከኞች attractive ቢሆንም መጨረሻ ላይ ግጭት ነው የሚያመጣው። ስለዚህ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አንድነት ኃይሎች ባይደነባበሩም ጥሩ አያደርጋቸውም። የአንድነት/ዜግነት ፖለቲካ ከባድ ቢሆንም ለሰላም ግዴታ ነው። ለዚህም ነው አብን የዜግነት ህገ መንግስት እንደ ግብ ያስቀመጠው።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!