ይህን የኤርሚያስ ለገሰ ቃለ ምልልስን እዩት!
https://www.youtube.com/watch?v=WB2enMd2Ilk&t=3990s
ሁለት ታላቅ ነገሮች ያስተምረናል፤
1) ሃላፊነት፤ ጸጸት፤ እና ንስሃ፤ ኤርሚያስ ከመጸሃፎቹ ሺያች ገንዘብ ለተለያዩ የኢህአዴግ ሰለቦች (እንደ አበበ ክንፈ ሚካኤል)መስጠቱን አውቅ ነበር (ይታወቃል)። ለምን ብሎ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ ሃላፊነት፤ ጸጸት እና ንስሃ ምን እንደሆኑ በጥሩ መንገድ የሚያስተምር ነው።
ኤርሚያስ ለኢህአዴግ በመስራቴ ኢህአዴግ ላደረገው ኃጢአቶች ህሊናዬ ስለሚወቅሰኝ ቢያንስ እንደ አቶ አበበ አይነቱን ተጎጂዎች በመርዳት ከራሴ ጋር እታረቃለሁ እና ላደረግኩት እንደ ካሳ ይሆናል ነው። ኤርሚያስ ማንንም አላሰረም አላሰቃየምም። ግን ሃላፊነት እንዳለበት አምኖ በሚመስለው መንገድ ይቅርታ እየጠየቀ ነው። ይህ የሚያስተምረን ሁላችንም በማድረግም ባለማድረግም ከመንግስት ሩቅ ብንሆንም በኢትዮጵያ ለተደረጉት ጥፋቶች ቢያንስ የተወሰነ ሃላፊነት እንዳለብን ነው። ታላቅ ትምሕርት ነው። ሁላችንም ይህን ትምሕርት ተምረን እራሳችንን እንደ ንፁሃን ከመቁጠር እንደ ኤርሚያስ ካሳ ለመክፈል ብናስብ ጥሩ ይመስለኛል።
2) የሰው ልጅ አስተዳደግ እና ጠቅላላ የኑሮ ጉዞ ለባህሪው እና ድርጊቱ አስተዋጾ አለው። ኤርሚያስ ስለ በረከት ስምዖን እና ባልደረባው ሽመልስ ሲጠየቅ «የሰው ልጅ ከመሬት ተነስቶ ክፉ አይሆንም» ብሏል። አስተዳደግ እና ታሪካዊ ምክንያቶች አሉ አለ። ይህን ሃቅ ሁላችንም ብናውቀውም ለመፍረድ ስንቸኩል እንረሳዋለን።
ይህ ሰውን አስተዳደግ እና ታሪክ ድርጊቱ ላይ ሚና አለው ስንል ለድጊታቸው ሰበበ ለማግኘት አይደለም። ለሁለት ምክንያት ነው፤ 1) ከመፍረድ እንዲቆጥበን ነው እና 2) መሰረታዊ ችግሮችን እንድናርም ነው። ለምሳሌ ከሰፈራችን አንድ ቤተሰብ ከማህበረሰቡ አላግባብ ተገልለው ኖረው ልጃቸው የደርግ/ህወሓት ጨቃኝ አሳዳጅ እና አሳቃይ ከሆነ ብዙ ሊገርመን አይገባም። ህብረተሰባችን እንደዚህ አይነት ሰዎችን የማይወልድ አይነት እንዲሆን መስራት እንዳለብን ያስታውሰናል።
አንድ መንግስት ጥሩ የሚሆነው እህታችን፤ ዘመዳችን፤ ጎረቤታችን፤ ወዘተ ሲመሩት ነው። ማለትም በህብረተሰቡ ክብር እና ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች ሲመሩት ነው። በህብረተሰቡ ላይ ቂም ያላቸው ሰዎች (እንደ መለስ ዘናዊ) መንግስትን ሲመሩ መንግስቱን የቂም መወጫ ነው የሚያደርጉት። የማህበረሰባችን ዋና ስራ ቂም ያላቸውን ሰዎች አለመፍጠር ነው፤ ሁሉንም አቅፎ መያዝ።
ለማንኛውም ይህን የኤርሚያስ ቃለ ምልልስ እዩት። በጣም አስተማሪ ነው።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!