Friday, 11 November 2022

ቅራኔአችሁን እንፍታላችሁ!

በተለይ ከ1997 ከቅንጅት ዘመን በኋላ ምእራባውያን ማለትም መንግስታት፤ ኤንጂኦዎች፤ ወዘተ ኢትዮጵያዊያን የግትርነት እና የቅራኔ ማባባስ ባህል አላቸው ብለው ያወሩ ነበር። በአንጻሩ እኛ ምእራባውያን በጠቅላላ የፖለቲካ ስልጣኔ በተለይም በቅራኔ መፍታት conflict resolution ጎበዝ ስለሆንን እናንተን ኢትዮጵያውያን እናስተምራችሁ አሉ። በርካታ ስብሰባዎች ትምሕርቶች በብዙ ገንዘብ ወጪ ተካሄዱ። ውጤቱ....

(በነገራችን ላይ እኔም በግሌ ይህ ባህላዊ ችግር አለን ብዬ አምኜ የፈረንጆቹን እርዳታ እንጠቀም ከሚሉት አንዱ ነበርኩኝ።)

ባህል ውስብስብ ነገር ነው። የእገሌ ባህል እንዲህ ነው የእገሌ ባህል እንዲያ ነው በደፈናው ማለት አይቻልም። ሁኔታዎች ሁሉንም ግለሰብም ቡድኖችንም ይቀይራል። እንሆ እነዚህ የቅራኔ መፍታት ባለሙያዎች ምእራባውያን ዛሬ ትክክለኛ ግትርነት ምን እንደሆነ እያሳዩን ነው። በከንቱ ዓለምን ንዩክሊየር ጦርነት ጫፍ ላይ አድርሰዋልና!

እኛ ኢትዮጵያውያን ወዲህ ወድያ ከማየት እራሳችንን ከምእራባውያን ይሁን ከምስራቃውያን ከማነጻጸር ወደ ራሳችን ተመልክተን በራሳችን እሴቶች ተጠቅመን እራሳችን ላይ ብንሰራ ይበጃል። ከሌሎች ጥሩ ነገር መማር ጥሩ ነው ተፈጥርዋዊም ነው። ግን ብዙ ጊዜ ይህ ከጥሩ ነገር መማር አልፎ ወደ ማነጻጸር ይሻገራል እና ሁለት «ኮምፕሌክሶች» ያሳድራል፤ 1) ሌሎች በደፈናው ይበልጡናል ብሎ ማሰብ 2) የራስን እሴቶችን አለማየት። እና ማነጻጸር አደገኛ ልምድ ይሆናል ከእውነታ እንድንርቅ ያደርገናል። ስለዚህ ብዙ ግራ ከኝ ሳንመለከት ችግራችንን በራሳችን በቂ የሆኑ እሴቶች መፍታት ጥሩ አካሄድ ይመስለኛል።

Friday, 4 November 2022

ስለ አማራ ብሔርተኝነት እንሟገት፤ በቅንነት!

ይህን አስመልክቶ መቼ ነው ለህዝብ ይፋ የሆኑ ውይይቶች የሚካሄዱት? ለአምራ ፖለቲካ ጤንነት ግልጽ ውይይት አስፈላጊ ይመስለኛል።

እኔ እንደሚገባኝ የአማራ ብሔርተኞች መሰረታዊ ችግር በእውነታ (reality) ሳይሆን በህልም/ቅዠት  የተመሰረተ ነው። የአማራ ብሔርተኝነት ህልም እንዲህ ነው፤ 

እነ አሳምነው ጽጌ (ነፍሱን ይማር) ወይንም ዛሬ እነ ዘመነ ካሴ በአማራ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ተጠቅመው 1) ወልቃይት/ራያን ይመልሱ ነበር 2) ቤኒሻንጉል፤ ወለጋ፤ አዲስ አበባ ወዘተ ያለውን አማራ ይጠብቅ ነበር 3) ፌደራል መንግስት ላይ ከባድ ትጽእኖ ያሳድሩ ነበር 4) አማራ ክልልን ያጎለብቱ ነበር 5) ሀገ መንግስቱን ያስቀይሩ ነበር።

ይህ ከእውነታ እጅግ የራቀ እንደሆነ ግልጽ ነው። ለ50 ዓመት ተደራጅቶ የማያውቅ አማራ በአንድ ሁለት ዓመት ተደራጅቶ ህወሓትን፤ ኦነግን፤ ፌደራል መንግስትን፤ ሱዳንን፤ ምእራባውያንን፤ ግብጽን ሁሉ ሊገጥም ይችላል ብሎ ማሰብ ቅዠት ነው። ሆኖም ስሜተን ስለሚቀሰቅስ እና ተከታይን ስለሚያበዛ የፖለቲካ ነጋዴዎች ይህንን ቅዠት በመሸጥ ለስልጣን ይጠቀሙበታል።

የአማራ ህዝብን ህልውና የሚጠብቅ በእውነታ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አካሄድ ነው። ይህም ህዝቡን በኢትዮጵያዊነት ማደራጀት ነው። ይህ አካሄድ የሚገነዘበው እውነታ ይህ ነው፤ የአማራ ትቅም የሚጠበቀው የመአከላዊ መንግስቱ በአግባቡ ከጠነከረ ነው። በተቃራኔው መአከላዊ መንግስቱ ከደከመ እና የጎሳ ፖለቲከኞቹ ከጠነከሩ አማራ ይጎዳል። ምክንያቱም 1) አማራ በዬ ክልል ተበትኗል እና 2) አማራው ከሌሎች ጎሳዎች የሚለየው ከባድ የትርክት ስራ ተሰርቶበት ጎሰኞቹ የአማራ ጥላቻን የፖለቲካ ንግድ አድርገውታል 3) አማራ በርካታ ታሪካዊ ጠላቶች አሉት። በዚህ ምክንያት የአማራ ህልውና ከመአከላዊ መንግስት ህልውና ጋር የተሳሰረ ነው። ኢትዮጵያዊነት የግዱ ነው።

«ኢትዮጵያዊነትን ሞክረን አልሆንም» የሚሉ አሉ። ይህ አስተያየት የሚመነጨው ከታሪክ አረዳዳት ስህተት ነው። በኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ኢትዮጵያዊነት (እንደ nation state) ገና እየተገነባ ነበር። በደምብ ሳይጠነክር እራሱ የኢትዮጵያዊነት ጎራው (በዚህ ውስጥ አማራው ሙሉ በሙሉ የተካተተበት ነበር) ተከፋፈለ እራሱ ላይ አብዮት አስነሳ። የኢትዮጵያዊነት ጎራው ገና ያልተገነባን ኢትዮጵያዊነትን አደከመ ማለት ነው። ደርግ ደግሞ አባባሰው። አብዮቱን ሲያፋፍም የኢትዮጵያዊነት የፖለቲካ ጎራውን (እራሱንም ጨምሮ) ይበልጥ አድክሞ የኃይል ሚዛኑ ተቅላላ ወደ ጎሰኞቹ ጎራ እንዲያመዝን አደረገ። መጨረሻ ላይ ስልጣንን ለጎሰኞቹ አስረከበ። ጎሰኞቹ ሲያሸንፉ አማራ መጎዳት ጀመረ።

ይህ ታክሪክ በግልጽ የሚያስተምረን የአማራ ህዝብ ህልውና ከኢትዮጵያዊነት የተሳሰረ መሆኑ ነው። ለዚህ ነው ለአማራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት የግድ ነው ያልኩት።

የግድ እንደሆነ ካመንን ቀጥሎ ጥያቄ እንዴት ነው ኢትዮጵያዊነትን ማጠንከር የምንችለው ነው። አዎን እጅግ ከባድ ስራ ነው። ለዚህም ነው አንዳንዱ አይቻልም ብሎ የሚሸሸው። የጎሳ ፖለቲካ የተፋፋመብት ሀገር ውስት ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን ከጎሰኞቹ እጥፍ ድርብ ብልህነት እና የፖለቲካ ችሎታ ያስፈልገዋል። በዚህ ምክንያት የአማራ ልሂቃን ማተኮር ያለበት ይህ ከባድ ስራ ላይ ነው። ህዝቡን በቀላሉ ስሜት ውስጥ የሚከተው ግን መጨረሻ ላይ ገደል የሚከተው ቀላል ፖለቲካን ትቶ ወደ ከባዱ ግን የግድ የሆነ ኢትዮጵያዊነት ስራ መግባት አለበት። 

የዐቢይ አህመድ መንግስትን መደገፍ እና ውስጡ ሆኖ መስራት አንዱ የዚህ ስራ ስትራቴጂ ነው። መአከላዊ መንግስቱ መጠንከር አለበት። ሀገረ መንግስቱ (nation state) መጠንከር አለበት የጎሰኞቹ ጎራም ይሁን የውጭ ጠላቶችም በቀላሉ ሊያጠቁ እንዳይችሉ። ስለዚህ መንግስት ምንም ችግሮች ቢኖሩት ለምጉዳት ይበልጥ ለማፍረስ መስራት የለብንም። መንግስትን መገንባት ነው ያለብን በተቻለ ቁጥር በኛ ፍላጎት። ይህ ስትራቴጂ የአማራ ህዝብን ይበጃል ብቻ ሳይሆን ለህልውናው የግድ ነው።

ሁለተኛ ስትራቲጂ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር መግባባት የግድ ነው ኢትዮጵያዊነትን ለማጠንከርና ሀገር መንግስቱንም ለማጠንከር። ሰጦ ገብ መቻል አለብን። በሶፍት ፓወር (መገናኛ ብዙሃን በመቋቋም፤ ቋንቋ በመማር፤ ወዘተ) ሌሎች ብሄረሰቦች ላይ መልካም ተጸኖ ማድረግ መቻል አለብን። ጎሰኞቹ አማራን በአማርኛ ሚዲያዎቹ እንደሰበኩ ነው አማራው ግን ወደነሱ ጎራ አይገባም! ይህ መቀልበስ አለበት። በታሪክ ቁርሾዎች በግልጽ መነጋገር እና መስማማት ያስፈልጋል።  

Defensive መሆን አያስፈልግም። ለኢትዮጵያዊነት ተብሎ የሌሎችን ምልከታ በትህትና መቀበል አለብን። በነዚህ አካሄዶች የአማራ ልሂቃን እና ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በተለይም ከለዘብተኞች ጋር ትብቅ ትስስር እንዲኖረን መስራት የግድ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ከባድ ስራ እንደሆነ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ግን ለአማራ ህዝብ የግድ ነው። ሌላ አማራጭ የለውም ታሪክ ይህንን ነው ያዘጋጀለት። ስለዚህ ወደ ስራ መግባት ነው እንጂ ስራን ሸሽቶ ወደ «የእጽ ፖለቲካ» የሆነው የአማራ ብሔርተኝነት መግባት የአማራ ህዝብ ሞት ንወ የሚሆነው።

Wednesday, 2 November 2022

FUD

 Written February 2022


አንድ የፕሮፓጋንዳ ዘዴ Fear Uncertainty Doubt (FUD) ይባላል። የዚህ ዘዴ አላማ አንድ ህብረተሰብ በፍርሀት፤ በአለማረጋጋትና በጥርጣሬ መንፈስ እንዲሞላ ነው። የአንድ ህብረተሰብን ስነ ልቦና በዚህ መንፈስ ከተሞላ የገዛ ራሱን ሸባና አቅመ ቢስ ያደርጋል። ከዛ በቀላሉ ይገዛል።
በተለይ ከነጭና ቆይ ሽብር በሗላ በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው ህብረተሰብ ስነ ልቦናው በፍርሀትና ጨለምተኝነት ተሞላ። ፖለቲካ ኮሬንቲ ነው ብሎ ከምንም አይነት መተባበርና መደራጀት ሸሸ። እንኳን በዘዴና በብልህነት በየዋሕነትም ለደህንነቱ መታገል አቃተው።
የዚህ ህብረተሰብ ጠላቶች ይህ ስነ ልቦናው ገብቷቸው ህብረተሰቡን በቀላሉ ለመግዛት FUD ፕሮፖጋንዳን ተጠቀሙ። ወደ ፍርሀት፤ አለመረጋጋትና ጥርጣሬ ያመዘነ ህዝብን ትንሽ ገፋ ካርግነው ወጥመድ ውስጥ ገብቶ ይቀራል ብለው አበቡ እንዳሉትም ሆነ።
የ FUD ዘዴ ቀልጣፋነት ዋናው ምክነያት የመቀጣጠል ባህሪው ነው። እንደ ቫይረስ ይሰራል። ይህ ማለት አንዴ ህብረተሰቡን ፍረሀት፤ አለሚጋጋትና ጥርጣሬን ካሳቀፍነው ህብረተሰቡ እራሱ እርስ በርሱ ፕሮፖጋንዳውን ያሰራጭል! የጠላት ስራ ይቀላል።
ባለፈው 30 ዓመት ዛሬም ይህ ነው በኢትዮጵያዊነት ጎራው ሲከሰት የታየው። ባለው በነባራዊው ሁኔታ ደስተኛ ያልሆኑት ንግግራቸው መልእክቶቻቸው አሉታዊ ናቸው። ከሌ እየጎዳን ነው፤ ከሀዲ ነው፤ እነሱ እየመጡብን ነው፤ ደህና ሰው የለም፤ አለቀልን ፤ ወዘተ። እነዚህ መልእክቶች የጠላትን የFUD ፕሮፓጋንዳ የሚያስፈጽሙ ናቸው። ህዝብን በቀላሉ እንዲገዛ የሚያደርጉ ናቸው።
ህብረተሰቡ ለራሱ ሰላም እንዲቆምና እንዲታገል የሚፈልጉ የFUD ተቃራኒ መልእክቶችን ነው ማስተላለፍ የለባቸው።
ቀጥታ ምሳሌ ልሰጣችሁ። ብልጽግና አማራንና ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እየጣላት ነው ብለው የሚያምኑት ዛሬ ምንድነው የፕሮፖጋንዳ መልእክቶቻቸው ምንድ ነው መሆን ያለበት? ዛሬ ከሞላ ጎደል 100% መልእክቶቻቸው አሉታዊ ነወ፤ ባጭሩ "ብልጽግና የጠፋናል" ነው። የFUD መልእክት ነው ህዝቡ ተስፋ ቆርጦ ወደ ተግባር እንዳይሄድ ያደርገዋል። በተዋራኒው 100% መልእክቱ መሆን ያለበት ህብረት ፍጠር፤ ተደራጀ፤ እርስ በርስ ተዋወቅ፤ አንድ ሁን፤ ተዘጋጅ፤ ወዘተ። ይህ መልእክት የህዝቡን ስነ ልቦና ከተጽእኖ ተደራጊ ወደ ተግባረኛ ይቀይረዋል። ቤቱ ቁጭ ብሎ ከሚያዝን ወደ ራስ ማዳን ስራ እንዲገባ ይገፋፈዋል። ይህ ነው የሚፈለገው።
በግሌ መንግስት በጎብዝም ባይረባም በኢትዮጵያዊነት የሚያምነው ህብረተሰብ ወደ ስራ ካልገባና ካልተደራጀ ከባድ ጉዞ ነው የሚሆነው። በFUD የተጠመደ ህዝብ ለራሱ አደጋ ነው።

Tuesday, 25 October 2022

የኩርፍያ ፖለቲካ

«እነ ስብሐት ነጋ ከተፈቱ ጀምሮ የአዲስ አበባ ህዝብ በዐቢይ ላይ አክሩፏል። ሮንድ ማድረርም አቆመ» ተባልኩኝ።

ይህ የፖለቲካችንን መሰረታዊ ችግር ያሚገልጽ አባባል ነው። ህዝቡ ማድረግ የነበረበት፤

1. ተቃውሞውን በሚገባው መግለጽ መንግስት እንዲሰማ እና እንዲገባው

2. እንደዚህ አይነት ነገር እንዳይደገም የመንግስት ስራተኞች፤ ህዝብ ወኪሎች፤ መሪዎችን መወትወት

ይህን ከማድረግ ፋንታ ህዝቡ ምን አደረገ፤

1. መንግስትን በሚያዳክም መልኩ እና ጠላትን በሚያጎለብት መልኩ መንግስትን ተቸ!

2. አክሩፎ እንደ ህጻን እራሱን የሚጎዳ ድርጊቶች ፈጸመ፤ ለምሳሌ አካባቢውን መጠበቅ ተወ!

ለ45 ዓመት በላይ ፖለቲካ ያቃጠለው ህዝብ እንደዚህ የፖለቲካ ደንቆሮ ይሆናል። የመንግስትን እርምጃ ለመቃወም የራሱን ጥቅም ይጎዳል! አካባቢ መጠበቅ ሮንድ ማድረግ ህዝቡን እጅግ ጠቅሟል። ደህንነትን እና አብሮነትን ጨምሯል። ህዝቡ ለዚህ መስክሯል። ስለዚህ ለራሱ ጥቅም ብሎ እነዚህን ስራዎች መቀጠል ነበረበት። ይህ ሎጂካል ነው። ግን ይህን ከማድረግ መንግስትን አክሩፍያለው ብሎ እራሱን መጉዳት ጀመረ።

ህወሓት ይሁን ሌሎች በቀላል ወሬ በህዝባችን የሚጫወቱት ለዚህ ነው። አህያ የሚሉንም ለዚህ ነው። ፖለቲካ አይገባውም። የራሱን ጥቅም አያውቅም። በቀላሉ ከምነግስት ልናፋታው እንችላለን ነው እነ ህወሓት የሚያስቡት። እንሆ ለ27 ዓመት የገዛነው ደንቆሮ ስለሆነ ነው በይፋ የሚሉት።

ሀገራችን ሰላም እንዲኖራት ይህን ነገራችንን ማሻሻል አለብን። መንግስት እያንዳንዱን የፈለግኩት ነገርን ካላደረገ ይፍረስ የሚለውን የመሃይ አስተሳሰብ እንዲጠፋ ማድረግ አለብን። ቀላል ዘመቻ አይሆንም።

Monday, 24 October 2022

ስደተኛን መቀበድ፤ በጎነት ወይንም ጥቅም

የዋህ ስለሆንን የካናዳ መንግስት የህወሓትን መሪዎች በስደተኝነት ከተቀበለ ካናዳ እንዴት በጎ አገር ነው ብለን እናስባለን። የምዕራባውያን አገራት ፕሮፓጋንዳ በዓስለም ታሪክ አንደኛ መሆኑ የሚመሰክረው እንዴት ለራሳቸው ጥቅም የሚያደርጉትን ነገር እንደ በጎነት አድርገው የማሳየት እና ሌሎችን የማሳመን ችሎታቸው ነው!

አንድ አገር የሌአ እገር የተሰደደ መሪ የሚቀበለው ዋጋ ስለሚያገኝበት ነው። አንድ፤ ብዙ እውቀት እና ችሎታ ያለው ሰው ያገኛል። ይህ ሰው እውቀቱን፤ ሚስጠሮችን፤ ምክሮችን ለአዲስ ባለሟሎቹ ይሰጣል! ሁለት፤ የተቀባይ አገሩን «በጎነት» ፕሮፓጋንዳ ያስመሰክራል።

የህወሓት ያረጁ መሪዎች ለካናዳ ምን ይሰሩለታል ብላችሁ ትጠቅቁ ይሆናል? እኛ የዋሆች ነን እኮ እንደዚህ በአጭሩ የምናስበው። ብልሃት ያላቸው መንግስታት እያንዳንዱን ትንሽ ነገር ዋጋ ይሰጡታል ያጠራቅማሉም። ሁሉም አብሮ ሲደመር ትልቅ ክምችት ይሆናል።

ዓለም እንደዚህ ነው እውነቱ። በዚ በኩል የዋህ ባንሆን ይሻላ።

መልካም አስተዳደር በአማራ ክልል

 እንደሰማሁት ከ2011 ጀምሮ በአማራ ክልል በቀበሌ ደረጃ ህዝቡ የሚያስተዳድረውን የመንግስት ሹማምንቶችን በገምገም እና ካስፈለገ ማጋለጥ ጀመረ። ህዝቡ «መንግስት የህዝብ ተወካይ እና አገልጋይ ነው» ይሚለው መርህ ገብቶት መርህውን በተግባር ማዋል ጀመረ። መልካም አስተዳደር እንዲኖር እኛ እንደ ህዝብ ስራ መስራት አለብን ሃላፊነትም አለብን ብሎ አመነ። ጥሩ ንቃት ነው።

ይህን ተከትሎ ህዝቡ ሙሰኞችን መጠቆም እና ማጋለጥ ጀመረ። ግን እንደሰማሁት መንግስት ሙሰኞቹን ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ ወደ ሌላ ቦታ ወስዶ ሌላ ብዙ ጊዜ የተሻለ ሹመት ሰጣቸው። ህዝቡ ይህንን ተመልክቶ ታዝቦ ተስፋ ቆረጠ። በአስተዳደሩ ሃላፊነት አለብኝ ማለት ተወ እና ወደ ድሮ «አክሩፎ ዝምታ» ገባ። ሙስናው እንደገና ጀመረ።

በዚህ ታሪክ ማን ተጎዳ ብለን ከጠየቅን መልሱ ግልጽ ነው፤ ህዝቡ እና ክልሉ ነው ተጎጂው። መፍትሄ ደግሞ ከተጎጂ ነው መመንጨት ያለበት። መፍትሄው ቀላል ነው። ህዝቡ የኢ-ሙስና ትግሉን መቀታል እና ማጠንከር አለበት። ልሂቃኑ፤ ሚዲያ እና «አንቂው» ደግሞ ትግሉን መደገፍ አለበት። የፍርድ ሂደቱን ተከታትሎ ሙሰኞች የት እንደደረሱ ማጋለጥ እና ተካውሞ ማስነሳት አለበት። ተቃውሞ መንግስት ላይ ሳይሆን ሙሰኞቹ እና የሙሰኞቹ አገልጋዮች ላይ ማነጣጠር አለበት። «መንግስትን ስለምንደግግ ከነዚህ መንግስትን የማይወክሉ ሙሰኞች ልናጸዳው ይገባል» አይነት የስራ መፈክር (mission) ሊኖረው ይገባል።

ለአንድ ህብረተሰብ ጥንካሬ መልካም አስተዳደር ቁልፍ ነው። መተማመን ቁልፍ ነው። አንድነት ቁልፍ ነው። አለነዚህ ህዝቡ የተበታተነ እና ግለኛ ይሆናል ለጠላቶች ተጋላጭ ይሆናል። 

የአማራ ልሂቃን በዚህ ዋና ጉዳይ ላይ በሙሉ አቅሙ ቢሳተፍ እራሱንም ህዝቡንም ይጠቅማል። ሌሎች የማይጥቅሙ የሚጎዱ አጄንዳዎችን ትተን።