ይህን አስመልክቶ መቼ ነው ለህዝብ ይፋ የሆኑ ውይይቶች የሚካሄዱት? ለአምራ ፖለቲካ ጤንነት ግልጽ ውይይት አስፈላጊ ይመስለኛል።
እኔ እንደሚገባኝ የአማራ ብሔርተኞች መሰረታዊ ችግር በእውነታ (reality) ሳይሆን በህልም/ቅዠት የተመሰረተ ነው። የአማራ ብሔርተኝነት ህልም እንዲህ ነው፤
እነ አሳምነው ጽጌ (ነፍሱን ይማር) ወይንም ዛሬ እነ ዘመነ ካሴ በአማራ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ተጠቅመው 1) ወልቃይት/ራያን ይመልሱ ነበር 2) ቤኒሻንጉል፤ ወለጋ፤ አዲስ አበባ ወዘተ ያለውን አማራ ይጠብቅ ነበር 3) ፌደራል መንግስት ላይ ከባድ ትጽእኖ ያሳድሩ ነበር 4) አማራ ክልልን ያጎለብቱ ነበር 5) ሀገ መንግስቱን ያስቀይሩ ነበር።
ይህ ከእውነታ እጅግ የራቀ እንደሆነ ግልጽ ነው። ለ50 ዓመት ተደራጅቶ የማያውቅ አማራ በአንድ ሁለት ዓመት ተደራጅቶ ህወሓትን፤ ኦነግን፤ ፌደራል መንግስትን፤ ሱዳንን፤ ምእራባውያንን፤ ግብጽን ሁሉ ሊገጥም ይችላል ብሎ ማሰብ ቅዠት ነው። ሆኖም ስሜተን ስለሚቀሰቅስ እና ተከታይን ስለሚያበዛ የፖለቲካ ነጋዴዎች ይህንን ቅዠት በመሸጥ ለስልጣን ይጠቀሙበታል።
የአማራ ህዝብን ህልውና የሚጠብቅ በእውነታ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አካሄድ ነው። ይህም ህዝቡን በኢትዮጵያዊነት ማደራጀት ነው። ይህ አካሄድ የሚገነዘበው እውነታ ይህ ነው፤ የአማራ ትቅም የሚጠበቀው የመአከላዊ መንግስቱ በአግባቡ ከጠነከረ ነው። በተቃራኔው መአከላዊ መንግስቱ ከደከመ እና የጎሳ ፖለቲከኞቹ ከጠነከሩ አማራ ይጎዳል። ምክንያቱም 1) አማራ በዬ ክልል ተበትኗል እና 2) አማራው ከሌሎች ጎሳዎች የሚለየው ከባድ የትርክት ስራ ተሰርቶበት ጎሰኞቹ የአማራ ጥላቻን የፖለቲካ ንግድ አድርገውታል 3) አማራ በርካታ ታሪካዊ ጠላቶች አሉት። በዚህ ምክንያት የአማራ ህልውና ከመአከላዊ መንግስት ህልውና ጋር የተሳሰረ ነው። ኢትዮጵያዊነት የግዱ ነው።
«ኢትዮጵያዊነትን ሞክረን አልሆንም» የሚሉ አሉ። ይህ አስተያየት የሚመነጨው ከታሪክ አረዳዳት ስህተት ነው። በኃይለ ሥላሴ አገዛዝ ኢትዮጵያዊነት (እንደ nation state) ገና እየተገነባ ነበር። በደምብ ሳይጠነክር እራሱ የኢትዮጵያዊነት ጎራው (በዚህ ውስጥ አማራው ሙሉ በሙሉ የተካተተበት ነበር) ተከፋፈለ እራሱ ላይ አብዮት አስነሳ። የኢትዮጵያዊነት ጎራው ገና ያልተገነባን ኢትዮጵያዊነትን አደከመ ማለት ነው። ደርግ ደግሞ አባባሰው። አብዮቱን ሲያፋፍም የኢትዮጵያዊነት የፖለቲካ ጎራውን (እራሱንም ጨምሮ) ይበልጥ አድክሞ የኃይል ሚዛኑ ተቅላላ ወደ ጎሰኞቹ ጎራ እንዲያመዝን አደረገ። መጨረሻ ላይ ስልጣንን ለጎሰኞቹ አስረከበ። ጎሰኞቹ ሲያሸንፉ አማራ መጎዳት ጀመረ።
ይህ ታክሪክ በግልጽ የሚያስተምረን የአማራ ህዝብ ህልውና ከኢትዮጵያዊነት የተሳሰረ መሆኑ ነው። ለዚህ ነው ለአማራ ህዝብ ኢትዮጵያዊነት የግድ ነው ያልኩት።
የግድ እንደሆነ ካመንን ቀጥሎ ጥያቄ እንዴት ነው ኢትዮጵያዊነትን ማጠንከር የምንችለው ነው። አዎን እጅግ ከባድ ስራ ነው። ለዚህም ነው አንዳንዱ አይቻልም ብሎ የሚሸሸው። የጎሳ ፖለቲካ የተፋፋመብት ሀገር ውስት ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን ከጎሰኞቹ እጥፍ ድርብ ብልህነት እና የፖለቲካ ችሎታ ያስፈልገዋል። በዚህ ምክንያት የአማራ ልሂቃን ማተኮር ያለበት ይህ ከባድ ስራ ላይ ነው። ህዝቡን በቀላሉ ስሜት ውስጥ የሚከተው ግን መጨረሻ ላይ ገደል የሚከተው ቀላል ፖለቲካን ትቶ ወደ ከባዱ ግን የግድ የሆነ ኢትዮጵያዊነት ስራ መግባት አለበት።
የዐቢይ አህመድ መንግስትን መደገፍ እና ውስጡ ሆኖ መስራት አንዱ የዚህ ስራ ስትራቴጂ ነው። መአከላዊ መንግስቱ መጠንከር አለበት። ሀገረ መንግስቱ (nation state) መጠንከር አለበት የጎሰኞቹ ጎራም ይሁን የውጭ ጠላቶችም በቀላሉ ሊያጠቁ እንዳይችሉ። ስለዚህ መንግስት ምንም ችግሮች ቢኖሩት ለምጉዳት ይበልጥ ለማፍረስ መስራት የለብንም። መንግስትን መገንባት ነው ያለብን በተቻለ ቁጥር በኛ ፍላጎት። ይህ ስትራቴጂ የአማራ ህዝብን ይበጃል ብቻ ሳይሆን ለህልውናው የግድ ነው።
ሁለተኛ ስትራቲጂ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር መግባባት የግድ ነው ኢትዮጵያዊነትን ለማጠንከርና ሀገር መንግስቱንም ለማጠንከር። ሰጦ ገብ መቻል አለብን። በሶፍት ፓወር (መገናኛ ብዙሃን በመቋቋም፤ ቋንቋ በመማር፤ ወዘተ) ሌሎች ብሄረሰቦች ላይ መልካም ተጸኖ ማድረግ መቻል አለብን። ጎሰኞቹ አማራን በአማርኛ ሚዲያዎቹ እንደሰበኩ ነው አማራው ግን ወደነሱ ጎራ አይገባም! ይህ መቀልበስ አለበት። በታሪክ ቁርሾዎች በግልጽ መነጋገር እና መስማማት ያስፈልጋል።
Defensive መሆን አያስፈልግም። ለኢትዮጵያዊነት ተብሎ የሌሎችን ምልከታ በትህትና መቀበል አለብን። በነዚህ አካሄዶች የአማራ ልሂቃን እና ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋር በተለይም ከለዘብተኞች ጋር ትብቅ ትስስር እንዲኖረን መስራት የግድ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከባድ ስራ እንደሆነ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ግን ለአማራ ህዝብ የግድ ነው። ሌላ አማራጭ የለውም ታሪክ ይህንን ነው ያዘጋጀለት። ስለዚህ ወደ ስራ መግባት ነው እንጂ ስራን ሸሽቶ ወደ «የእጽ ፖለቲካ» የሆነው የአማራ ብሔርተኝነት መግባት የአማራ ህዝብ ሞት ንወ የሚሆነው።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!