Showing posts with label ርእዮተ ዓለመ. Show all posts
Showing posts with label ርእዮተ ዓለመ. Show all posts

Friday, 16 February 2018

ጨቋኝና ተጨቋኝ

እንደተረዳሁት ባለፈው ባወጣው መግለጫ ኦህዴድ የኢትዮጵያ መሰረታዊ የጭቆና ታሪክ የ«መደብ ጭቆና» ነበር እንጂ የ«ብሄር ጭቆና» አልነበረም ብሏል። ለዚህ አቋማቸው ኦህዴድን አደንቃለው አመሰግናለውም። ከረዥም ዓመታት የተሳሳተ እምነታቸው መቀየር ከባድ ነውና ጥንካሬና ህሊና ይጠይቃል። ዛሬ በሃገራችን ያለውን ከፍተኛና ኢ-ጤናማ የጎሳ ውጥረትንም ተገንዝበው የተሳሳተ ርእዮተ ዓለማቸውን ገምግመው ሃሳባቸውን ቀይረው ይህንን በይፋ ማውጣታቸው ትልቅ ነገር ነው። ደግሞ ከሌሎች አጋር ፓርቲዎቻቸው ቀድመው ይህን ማድረጋቸውም ሊደነቅላቸው ይገባል። እነ ለማ መገርሳ ለኢትዮጵያዊነት ታላቅ አስተዋጾ እያደረጉ ነው።

ሆኖም ይህ ዜና በሃገራችን መሰረታዊ የሆነ አሳዛኝ አስተሳሰብ አሁንም እንዳለ ይገልጻል? «ጨቋኝ» እና «ተጨቋኝ» እራሱ የተሳሳተ ቋንቋ ነው። ጽንሰ ሃሳብ የመጣው ከውሸትና ኢባህላዊ የሆነ የምእራባዊ የኮምዩኒስት አስተሳሰብ የመነጨ ነው። እስቲ አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ተመልሰን ለምንድነው የሰው ታሪክ በ«ጨቋኝና ተጨቋኝ» የሚለው አስተሳሰብ መወሰን ያለበት? እንደዚህ አይነቱ አስተሳሰብ በሃሳብም ደረጃ በተግባርም ግጭት፤ ቅሬታ፤ ቂም፤ ጦርነት፤ ግድያ፤ አብዮት ወዘተ የሚያስገድድ ነው። አንድነት፤ ፍቅር፤ ይቅርታ፤ ትህትና፤ መስማማት ወዘተ የሚቃረን አስተሳሰብ ነው።

አልፎ ተርፎ ማን ግለሰብም ህብረተሰብም ፍፁም ንፁሃን ፍፁም ጥፋተኛ የሆነ የለም። እያንዳዳችን ጨቁነናል ተጭቁነናል፤ በድለናል ተበድለናል፤ ወደናል ተወደናል፤ ተስማምተናል ተጣልተናል፤ ተሳስተናል ስታታችንን አምነን ይቅርታ ጠይቀናል፤ ቂም ይዘናል ይቅርታን ተቀብለናል። በዚህ ዓለም እኔ ነኝ ንጹ ተጨቋኝ የሚል የራሱን ጥፋት ስለማይመለከት ወደ ከባድ ጥፋጡስት ይገባል ሰፊ በደልም ይፈጽማል።

በዚህ ጉዳይ ታላቅ የሩሲያ ደራሲ አለክሳንደር ሶልዠኒትሲን ያሉትን በደምብ ሊገባን ይገባል፤
ከእስርቤታችን አልጋ የሆነው የበሰበሰው ገለባ ላይ ጋደም ብዬ ነው ለመጀመርያ ከውስጤ የበጎ መንፈስ የተሰማኝ። ቀስ በቀስ መረዳት የጀመርኩት ይህ ነው፤ ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር በሀገሮች፤ መደቦች፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መካከል አይደለም የሚያልፈው፤ ይህ መስመር የሚያልፈው በያንዳንዱ የሰው ልብ መኻል ነው። መስመሩ እድሜአችን በሙሉ ከውስጣችን ወደፊት ወደኋላ ይላል። በክፉ የተሞሉ ልቦችም ቢያንስ ቅንጣት ያህል ጥሩነት ይኖራል፤ ከሁሉም ጥሩ ከሚባለውም ልብ ከአንድ ጥጓ ትንሽ ክፉነት ይኖራል።
በየቦታው እየዞሩ ያሉ ክፉ ስራ የሚሰሩ ክፉ ሰዎች ቢኖሩና እነሱን ከኛ መለየትና ማጥፋት ብቻ ቢሆን ኖሮ እንዴት ቀላል ነበር? ግን ጥሩና ክፉን የሚለየው መስመር ከያንዳንዱ የሰው ልጅ ልብ መካከል ነው የሚያልፈውና ማን አለ ከራሱ ልብ ቁራጭ ቆርጦ ለማጥፋት ፈቃደኛ ይሆነ?
ሶልዘኒትሲን ኮምዩኒስት የነበሩ ወታደር የነበሩ ስታሊን ለዓመታት በሞት እስር ቤት (ጉላግ) ያሰራቸው ከሩሲያ ወደ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታቸው የተመለሱ የሩሲያ ጀግና ነበሩ። ተጨቋኝ ነኝ ማለት የሚገባቸው ነበሩ። ለሃገረቸው ጦርነት ተዋግተው በማግስቱ የታሰሩ ናቸው። አለምንም ጥርጥር ተጨቋኝ ነኝ ማለት የሚገባቸው ነበር። ግን እስር ቤት የሌሎችን ሳይሆን የራሳቸውን ኃጢያት እንዲገለጽላቸው አደረገ! የሰው ልጅ እውነተኛ ባሕርይ እንዲረዱ አደረገ። የሰው ልጅ ችግርም እንዴት መቅረፍ እንደሚቻል ገባቸው። በጦርነት፤ በማስወገድ፤ በማባረር፤ በመወገን ሳይሆን በንስሃ፤ በመስማማት፤ በመከባበር፤ በመቻቻል ነው።

ይህ ሩሲያዊ ሶልዠኒትሲን የዘመኑን «ጭቋኝና ተጨቋኝ» አስተሳሰብን ትተው የእውነትን ባህላዊ የኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ነው የገለጹት። ሩሲያዊው ኦርቶዶክስ ባህላችንን ያስታውሱን። ለምንናውም የኢትዮጵያ ባህል፤ ማንኛውም ሃይማኖት፤ ይህ የ«ጨቋኝና ተጨቋኝ» ርእዮተ ዓለም በአድ ነው። በአድ ነው። ሚስኪኖቹ የጃንሆይ ተመሪዎች ወደ ሃገራችን ከምእራብ ሃገራት ያመጡት መርዝ ነው። መርዙን እናውጣው። ወደ እራሳችን እንመለስ።