Monday, 29 August 2016

የኢትዮጵያ ብሄርተኞች፤ አርፍደን ቢሆንም ነቅተናልን?

2008/12/12 ዓ.ም. (2016/8/18)

በመጀመርያ ለመላው ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርታዬን ላቀርብ እወዳለሁ። የሀገሬ የኢትዮጲያ ወዳጅ በአንድ ኢትዮጵያ የማምን የኢትዮጲያ ብሄርተኛ እንደመሆኔ ለ60 ዓመት በላይ ሀገሬን በድያታለሁና። ፖለቲካዋ እንዲበላሽ ፈቅጄ ህዝቧ እንዲጎሳቆል አድርግያለውና።

ልጆቻችን ሀገራችንን የሚጠቅም የሙያ ትምህርት እንዲማሩ ብለን ወደ ፈረንጅ ሀገራት ስንልካችረው ተገቢውን ጥንቃቄ ሳናደርግ ቀርተናል ። በዚህ ምክንያት አባቶቻቸውን፤ ባህላቸውን፤ ትውፊታቸውን እንዲንቁ የሚያረግ ሀገር አጥፊ የሆነ ርዓዮት ዓለም እንደ ጣዖት እያማለኩ ተመለሱ። እኛም «የተማረ ይግደለኝ» እያልን ለሚያመጡት አደጋ ታውረን ተቀበልናቸው። 

ይህ እንዳለ ሆኖ ተገቢ የሆኑትን የመሬት የቋንቋ ወዘተ የፖለቲካ ጉዳዮችን በአግባቡ መመለስ እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች አቅቶን ህዝብ ጨራሽ የሆነ የተማሪ ንቅናቄና የወታደር ጥምረት ስልጣን እንዲይዝ አደረግን። የኛ ኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሆነውን ጎራ ከፖለቲካ ተሰደድን ወይም ኢዲዩ ነኝ፤ እህአፓ ነኝ፤ ደርግ ነኝ ወዘተ እያልን እርስ በርሱ ተለያየንም ተጨራረስንም። በመጨረሻ የወለድነው የደርግ መንግስት ሀገራችንን አመሰቃቅሎ ህዝብን በስመ ኢትዮጵያዊነት ገድሎ አንዳንድ ወገኖቻችንን ወደ እነ ሻእብያ፤ ህወሓት፤ ኦነግ ወዘተ አይነት የጎሳ ድርጅቶች እንዲሽሸጉ አድርጎ ሀገሪቷን ለነዚሁም አስረከበ። 

1983 ዓ.ም. ሲደርስ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት እንደ ፖሊቲካ ኃይል የመጨረሻ ወድቆ ተገኘ። በፖለቲካ ድርግት ወይም ንቅናቄ መልክ አልነበረም። በመጽሔትና ለቅሶ ቤት ብቻ ቀርቶ ነበር። የኢትዮጵያ ህልውና በኃይል ያላቸው የጎሳ ብሄርተኞች እንደ ህወሓት ተወሰነ። እኛ የኢትዮጵያ ብሄርተኞች እራሳችንን በማጥፋት ሜዳውን ለነሱ ለወለድናቸው «የጠፉ ልጆች» ተውንላቸው። ታድያ ለዚህ ሁሉ ይቅርታ መጠየቅ አያስፈልግምን?!

ላለፉት የ60 ዓመታት የኢትዮጵያ የፖሊቲካ ችግሮችን የኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ወገንን ብቻ ጥፋተኛ ማድረግ ጉዳዩን ማቅለል እንደሆነ አላጣሁትም። ግን በኢትዮጵያ ብሄርተኞች ጥፋትና ድክመት ማተኮር የመረጥኩት አስተማሪ ስለሆነና የችግሮቹን መፍትሄ በግልጽ እንድናይና እንድንረዳ ስለሚጠቅመን ነው።

ለምሳሌ በተደጋጋሚ የሚነሳው ጥያቄ «ከአናሳ ብሄር የመነጨው ኢህአዴግ ለ25 ዓመት ስልጣን እንዴት ሊይዝ ቻለ» ነው። የዚህንም ጥያቄ መልስ ካገኘን ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው። ለዚህ ዋናው መልስ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሆነው የፖሊቲካ ጎራ ከኢትዮጵያ የፖሊቲካ ሜዳ ስለጠፋ ወይም ኃይል አላባ ስለሆነ ነው። የጠፋው ደግሞ በህወሓት እጅ ሳይሆን በራሱ እጅ ነው። የተማሪ ንቅናቄው የለኮሰው አብዮትና የደርግ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄርተኛ አመራርንና ልሂቃንን ሀገር ውስጥም ወደ ውጭም በታተናቸው። የኢትዮጵያ ብሄርተኛ የሆነው ብዙሃንም በደርግ ዘመን በነበረው ጭካኔ ተመርዞ «ፖሊቲካና ኮሬንቲ» እያለ ፖሊቲካን ዞር ብሎ ላለማየት ወሰነ።

በዚህ ምክነያት የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ሚዛን አጣ እስከ ዛሬም አጥቷል። ይህ እጂግ ዋና ነጥብ ነው። በታወቀው የ1983 ዓ.ም. የለንደን ሰብሰባ የተደራጀ ኃይል የነበራቸው ጎራዎች ሻእብያ ኢህአዴግና ኦነግ ነበሩ። ቢዚህ ምክነያት የኢትዮጵያ የወደፊት አካሄድን የወሰኑት፤ እንደ ህገ መንግስት አይነቱን መሰረታው ስምምነቶች ያቀናበሩት፤ የተወሰኑት የጎሳ ብሄርተኛ ድርጅቶች ናቸው። የኢትዮጵያ ብሄርተኛው ጎራ በመደራጀትና በኃይል ማጣት ምክንያት አልተሳተፈም።

ይህ ሲሆን ኢህአዴግና ሌሎቹ ትልቅ ስህተት አድርገዋል። ደርግና የኃይለ ስላሴ መንግስት መውደቃቸውና የኢትዮጵያ ብሄርተኞች የተደረጀ ኃይል ማጣጣቸው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት በብዙሃኑ ተቀባይነት እንዳጣ ያሳያል ብለው ገመቱ። ነገር ግን የተወሰኑ ወገኖች የኢትዮጵያ ብሄርተኝነትን ባለመፈለግ ደርግን ቢዋጉትም አብዛናው ህዝብ ደርግን የጠላው ስለ ሶሺአሊዝሙ ጭካኔው ወዘተ ነው። 

ሆኖም ይህ በኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የሚያምን ግን ደርግን የማይወድ ህዝብ ብፖሊቲካ ድርድሩ አልትቆጠርም አልተሳተፈም አልተወከለምም። ይባስ ብሎ ኢህአዴግ ለ 25ዓመታት ዋና ስራውን የኢትዮጵያ ብሄርተኞች (ወይም «ትምክህተኛና ነፍጠኖች» ብሎ የሰየማቸው) የፖሊቲካ ወገን እንዳይነሳ ማድረግ ነበር። ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፖሊቲካን ኢሚዛናዊ አድርጎ የዛሬው የፖለቲካ ችግሮች አንዱ ምክንያት ሆኗል። ለመድግም ያህል የኢህአዴግ ጥረት ብቻ ሳይሆን የጎራው እርስ በርስ መፋጀትና ሌሎቹ ከላይ የተጠቀሱት የታሪክ ምክነያቶች ናቸው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት የፖለቲካ ኃይል እንደመነምን ያደረጉት። 

በደምብ ማስተዋል ያለብን አናሳን የሚወክል አገዛዝ ህወሓት በተለይም አናሳ ጎሳን የሚወክል አገዛዝ ያለ ሌላው ህዝብ ፈቃድ መግዛት በፍጹም አይችልም። አናሳ ነውና በኃይል በመጨፍጨፍ በማሰር ወዘታ ብቻ ሊገዛ አይችልም። ስለዚህ ህወሓት የማይወክለው ህዝብ እርስ በርሱ እንዲጣላና እንዲከፋፈል ወይም በፖሊቲካ በፈቃደኝነት እንዳይሳተፍ የግድ ያስፈልገዋል። ይህ ካልገባን ወይም ካላመንን ኢህአዴግ በርካታውን የኢትዮጵያን ህዝብ ይወክላል ብለን አመነናል ማለት ነው! ይህን ደግሞ ኢህአዴግ እራሱ አያምንም።

አሁን ግን ይህ ያልተወከለው ህዝብ መሳተፍ የጀመረ ይመስላል። ከ25 ዓመት በኋላ በጎንደር በባህር ዳርና በመላው በአማራ ክልል የምናያቸው የህዝበ ሰልፎች የዚህ ምልክት ናቸው። እርገጥ ከዚህ በፊት የተለላዩ የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ስሜትን ያቀፉ እንቅሳቅሴዎች ለምሳሌ እንደ ቅንጅት አይነት ኖረው ያውቃሉ። እነዚህ ግን ወደ ኋላ ሄደን ስናያቸው በአብዛኛው በከተማ ህዝብ የተመኩና ውስጣቸው የተከፋፈለ ንቅናቄዎች ነበሩና በነዚህ ምክነያቶች ኢህአዴግ በቀላሉ ሊያጠፋቸው ችሏል። ወይም በተለያዩ ብልጥ የመርህ መልሶች እንደ «ልማት እንሰጣቹሃለን ስልጣና ጥቅማችንን አትንኩ እንጂ» የሚለውን እያራመዱ ተቃዋሚዎች የህዝብን ድጋፍን እንዲያጡ አደረጉ።

የዛሬው በአማራ ክልል የሚካሄደው የነፃነት እንቅስቃሴ ግን ከዚህ ታሪክ የተማረ ይመስላል። የአማራ ክልል ህዝብ በደፈናው የኢትዮጲያ ብሄርተኝነት ስሜት ያለው ነው፤ በአማራ ክልል አክራሪም ይሁን ለዘብተኛ የጎሳ ብሄርተኝነት በሞላ ጎደል የለም። እንሆ ለ25 ዓመታት የኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ይህ ሰፊ የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ጎራ ከሞላ ጎደል ከኢትዮጵያ ፕሊቲካ እራሱን አውጥቶ ይኖር ነበር። አሁን ግን ተነስቷልና የሚዘልቅ ከሆነ ኢህአዴግ በምንም መንገድ ልያቆመው አይችልም።

ለኢህአዴግ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ይቀሉታል። በእነዚህ ቦታዎች የተለያዩ ህዝቦች መደቦችና ጎሳዎች አሉና ጠንከር ያለ ጭቆና በማራመድ መከፋፈልን (ኦነግ ሊያርድህ ነው ወይም አማራ ሊገዛህ ነው ወይም ንብረትህ ሊወድምብህ ነው እያለ) ጥርጣሬንና ፍረሃትን አስፍኖ የፖሊቲካን እንቅስቃሴ መግደል ይችላል። በአማራ ክልል ግን እነዚህ መስፈርቶች የሉምና መከፋፈሉ ቀላል አይደለም። ኢህአዴግ ትልቅ የጭቆና እርምጃ ከወሰደ ደግሞ አማራውን በጎሳነቱ ያስተባብረዋልና ይህ የጎሳ ጦርነት ይጋብዛል። ከጥቂት የህወሓት አክራሪዎች በቀር የኢህአዴግ አመራር ይህን በደንብ ይረዱታል አይፈልጉትምም።

ሆኖም ኢህአዴግ እስቲ እንደልማዳችን ወይም ለ25 ዓመታት እንዳረግነው የኃይል እርምጃ በመጀመርያ እንውሰድና ውጤቱን እንየው ብሏል። የኢህአዴግ  ለዘብተኞችም ለአክራሪው ወገን እርምጃህን ሞክር ግን ካልሰራ መሪው ወደኛ እጅ ይገባል ብለው ተስማምተዋል። ንቅናቄው ካልቆመ  በየአቅጣጫው ለውቶች ይጅምራሉ። እያንዳንዱ የመንግስት የህብረተሰብም መዋቅሮች ውስጥ በተለይ ጦር ስራዊት ውስጥ ታላቅ ለውጦች ይኖራሉ። ከላይ የጠቀስኩት የተበላሸው የኢትዮጵያ የፖሊቲካ ሚዛን መስተካከል ይጀምራል። ከስንት ዓመታት በኋላ ከሀገር ፖሊቲካ የጠፋው የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ጎራ ሃላፊነቱን ተቀብሎ ድምጹን ያስከብራል። ይህ ሁኔታ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ድል ይሆናል የሀገሪቷን ፖሊቲካ ሁሉን አቀፍ በማድረጉና ወደ እውነታን የሚያንጸባረቅ ትክክለኛው ሚዛን በማስተካከሉ። ነገር ገን ይህ ዕድል ካለፈን…

ፑቲኖቻችን የት አሉ?

2008/12/6 ዓ.ም. (2016/8/12)

የሶቪዬት ህብረት ከወደቀ ብኋላ ምእራቡ ዓለም በተለይ አሜሪካ ሩሲያኖችን እንረዳችኋለን፤ ኤኮኖሚአችሁ እንዲታደስና እንዲያድግ እንረዳችኋለን፤ ወደ ዓለም ኤኮኖሚ በቀላሉ እንድትቀላቀሉ እናደርጋለን፤ የቀዝቃዛ ጦርንነትን ለማፍረስ ስለተባበራችሁን ሩሲያ በጠቅላላ እንድትበለጽግ እናደርጋለን ብለው ቃላቸውን ሰጡ። ነገር ግን ቃላቸውን አጥፈው በሩሲያ ሀገር አፍራሽና ህዝብ ጎጂ የሆነ አመራርና መርህ በሀገሪቷ እንዲሰፍን ገፋፉ። በዚህ ምክንያት የሩሲያ ህዝብ የአስር ዓመት በላይ የስቃይ ዘመን አሳለፈ። ስቃይ ስል ህዝቡ ደህይቶ የሚበላውን ያጣበት፤ ወንጀልና ሽብርተኝነት የሰፈነበት፤ ህዝቡ ጤና አጥቶ የአማካኝ የህይወት እድሜ ከ70 ወደ60 የወረደበት፤ ሙስናና የማፊያ (ትብብር ወንጀል) ሥረዓት የሞላበት ሀገር ሆና ነበር ሩሲያ።

በዚህ የሩሲያ ስቃይ ዘመን የሀገሪቷ መሪ ፕሬዚደንት ቦሪስ ዬልትሲን ነበሩ። በ1991ዓ.ም. ከስልጣን በፈቃዳቸው ወረዱና ምክትላቸውን ቨላዲሚር ፑቲንን ፕሬዚደንት እንዲሆን ወከሉ። የዬልትሲን ደጋፊዎች የሆኑት በመንግስት አመራር ውስጥ የነበሩት ትላልቅ ባለ ሀብቶች የውጭ ሀገር «ንጂኦ» አንቀሳቃሾች የምዕራብ ሀገር መንግስታት ሁሉም ፑቲን በአስተሳብም በርዕዮት ዓለምም በእምነትም የዬልትሲን ተቃራኒ እንደሆነ ዓገር ወዳጅ እንደሆነ አልጠረጠሩም ነበር! በኢትዮጵያ ሁናቴ ለማምሳሰል ያህል መለስ ዜናዊ ይልቃል ጌትነትን ወይም ሌላ ተቃዋሚ ሾሙ እንደማለት ነው!

ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እንዴት ዬልትሲንና ዙሪያቸው ያሉት መሪዎች ደጋፊዎች ባለሟሎችና የውጭ ሀገር መንግስታት የፑቲንን የእውነት ባህሪና አቋም አላወቁም? ምክንያቱ ቀላል ነው፤ ፑቲን እራሱን አላገለጠም። ማንነቱን በሚያስፈልገው መጠን ሰውሮ ነበር። ይልቁኑ በዬልትሲን መንግስት በተለያየ ቦታዎች ሲያገለግል ጎልማሳው ፑቲን በታታሪነትና በዓለቃን ማክበርና በተለይ ለዓለቃ ያለው ታማኝነት ነበር የሚታወቀው። ከአመራር ወስጥ ያሉትና ከየሀገሩ ገዥ የነበሩት ባለሃብቶች («የሩሲያ ቢሊዮኔሮች» የተባሉት) በደምብ ይግባባ ነበር። ከመጠን በላይ ብልጥም ፖሊቲካ የገባውም ነበር። በፍጹም አልተጠረጠረም!

ቨላዲሚር ፑቲን ፕሬዚደንትም ሲሆኑ የእውነት አቋሞቻቸውን ወድያው አላሳዩም። በመጀመርያ ስልጣናቸውን ቀስ በቀስ አጠናከሩ። ጓደኛ እንጂ ጠላት የማያፈራ መርህዎችን አራመዱ። አሸባሪዮችን አጠቁና የጦርሰራዊት የፖሊስና የጸጥታ ኃይሎችን ድጋፍ አረጋገጡ። ከምዕራብ ሀገሮች ጋር በጸረ ሽብርተኝነት ሩሲያ በደምብ እንድትተባር አደረጉና የምዕራብ መንግስታትንም ድጋፍ አገኙ። ከዚያ ቆይተው ፑቲን ስልጣናቸውን ካረጋገጡ በኋላ በዬልትሲን ዘመን በዝርፍያና በሙስና ያደጉት ባለሀብቶችን በማሳሰር በማሳመን ስልጣናቸውን ነጠቁ አጠፉ። እነዚህ እርምጃዎች የፑቲንን የህዝብ ድጋፍ መጠን በጣም እንዲልቅ አደረጉ (ስልጣን ከያዙ ጅምሮ ከ65 እስቀ 80 በመቶ ድጋር አላቸው)።

ከዬልትሲን ወደ ፑቲን የተካሄደው የሩሲያ ለውጥ ከሞላ ጎደል ሰላማዊ ነበር። እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚፈለገው ሰላማዊ፤ ማንም የማይጠቃበት፤ ሀገር የማይረበሽበት፤ ጥላቻ የማይሰፍንበት፤ ቅራኔ የምያሳንስና መግባባት ለዘብተኝነት መቻቻል የምያጠቃልል ለውጥ ነው።

እንደዚህ አይነት ለውጥ የሚመጣው ከዓብዮት ሳይሆን ከውስጣዊ ቀስ በቀስ የሚመጣ ለውጥ ነው። ለንደዚህ አይነት ለውት የነባር መንግስት ውስጥ በርካታ የለውጥ አጋሮች ያስፈልጋሉ፦ ፑቲኖች ያስፈልጋሉ! ሥርዓቱ ሲናጋ ውግያና ሁከት ለማምጣት ወደኋላ የማይሉ አክራሪዮች ስልጣን እንድይዙ ውይም በውሳኔ ላይ እንዲያመዝኑ ያደርጋል። ይህ እንዳይከሰት እነዚህ የውስጥ ለውጥ የሚፈልጉ ለዘብተኛ የሆኑት አስፈላጊ ናቸው። አክራሪውም በለዘብተኛው እንደተከበበ ሲያይ ግድ ይመለሳል።

ነገር ግን እንደዚህ ሰርጎ ገብተው የሚያገለግሉ ሰዎች የራሳቸውን ህልውና ለመጠበቅና ይበልጥ ረጅም አላማቸው እንዳይከሽፍ ብለው እራሳቸውን መደበቅ አለባቸው። እዚህ ላይ ብልጠት ያስፈልጋል። መሪዎቻቸውን መምሰል አለባቸው። አለጊዘው ስልጣናቸውና የስልጣን ድራቸውን በቂ ሳያስፋፉ ሳያጠነክሩ ጠንካራ አቋም መውሰድ የለባቸውም። እንደ ፑቲን ስያስፈልግ አንገታቸውን ደፍተው መኖር አለእባቸው። «እንደ እባብ ብልዖች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ» ውይም «ዛሬ ህይወትን ካጡ ወደፊት መታግል አይቻልም» እንደሚባለው።

በዚህ ጊዜ ብዙሐናም «ተቃዋሚዎች»ም ብልህ መሆን አለባቸው። ከውስጥ የስውር ጠቃዎሚዎች በይፋ እየተሟገቱ በስውር መተባበር አለባቸው። አንድ ነገር ማስታወስ አለብን፤ ዋናው የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ችግር የተሳትፎ ጉዳይ ነው። ህዝቡ መሪውን ሲጠላ ከመንግስት ወስጥ ከመሳተፍ ይርቃል። «ፖለቲካና ኮሬንቲ» የሚባለው ስሜት ያመዝናል። ይህ ማለት በርካታ የኢትዮጵያ ህዝብ ወገኑን ውይም የሃሳብ አጋሩን ከመንግስት ወስጥ የለም። በታችኞቹ የመንግስት አካሎችም እንደ ቀበሌና ወረዳ ለመሳትፍ አይፈልግም ቤተሰቡም ዘመዱም እንዲሳተፍ አይፈልግም። መንግስትን «ለሌሎች» ትቶት በብአድ እየተገዛ ነው። ይህ አስተሳሰብ ተገቢ የሆነ የታሪክ ምክንያት ቢኖረውም ትክክል አይደለምም እጅግ ጎጂም ነው። አለመሳተፍ አክራሪነትንና ዓብዮትን የሚጋብዝ ለዘብትኘትና ትብብርን ቦታ የሚያሳጣ አስተሳሰብ ነው።

«እንዴት ኢህአዴግ ውስጥ መስራት ይቻላል፤ ሕሊናን መሸጥ ወይም ጥቃትን መቀበል ያስፈልጋል» ሊባል ይችላል። ታድያ በሰሞኑን የጎንደር ተቃውሞ ላይ የኃይል እርምጃ እንዳይወሰድ ያደረጉት ማን ናቸው? አልፎ ተርፎ በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ወስጥ ያሉት በዝቅተኛ የስልጣን ደረጃ ያሉት ወታደሮች በአብዛኛው ማናቸው ከየት ናቸውም? በየቀበለውና ወረዳ የሚያስተዳደሩት (ከትግራይ ክልል በስተቀር) ማናቸው? የታወቀው ኢህአዴግን ለቆ የወጣው ኤርሚያስ ለገሰ ማን ነው? አምባሳደር ሆኖ በግዞት ወደ ቱርኪ የተላኩት አቶ አያሌው ጎበዜ ማን ናቸው? ለነገሩ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ማናቸው? እነዚህ በሙሉ የለውጥ አጋሮች ወይም ሁኔታዎች ሲፈቅዱ የለውጥ አጋሮች ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው!

መርሳት የለለብን የኢህአዴግ መንግስት የአናሳ መንግስት እንደሆነ ነው (በዚህ ካልተስማማን የህዝበ ድጋፍ አላቸው ብለን አመንን ማለት ነው!)። ኢህአዴግ መላ የኢትዮጵያን ህዝብን እንወክላለን ባይ ነው ግን ተቃዋሚዎችና በርካታ ህዝብ የትግራይ መንግስት ነው ብሎ ይከሰዋል። አናሳ ነው ብለን ከተቀበልን ማውቅ ያለብን አናሳ መንግስት ሀገርን መግዛት የሚችለው ሌላው ህዝብ ከፈቀደለትና በደምብ ከተባበረው ብቻ ነው! ኢህአዴግ እንደ ደርግ አለብልሃት በመጭፍለቅ ብቻ መግዛት አይችልም። ኢህአዴግ የሌላው አለመተባበር ውይም ከፖሊቲካ መራቅ ውይም በፈቃደኝነት መገዛት ያስፈልገዋል። ይህ ውነታን በግልፅ የሚያንጸባርቀው ኢህአዴግ ፓርቲውም ጦርሰራዊቱም በቁጥር ደረጃ በአብዛኛው የትግርኛ ተናጋሪ አለመሆኑ ነው።

ስለዚህ ኢህአዴግ ውስጥ ገብቶ ወዲያው ሳይሆን ከስ ብሎ ልውጥ ማምጣት ካልሆነም የለውጥ አጋር መሆን እንደሚቻል ግልፅ ነው። ህዝቡ ይግባ፤ ይሳተፍ፤ ሲያስፈልግ አንገቱን ደፍቶ እሺ ይበል፤ ቀስ ብሎ በስልጥ አብዛኛነትን ያረጋግጥና ጊዘው ሲደርስ ለውጥ ያመጣል።

ከፑቲን የምንማረው ትምህርት የህ ነው። ፑቲን ለዬልትሲን መንግስት ሲያገለግል ብቸኛ የውስጥ ተቃዋሚ አልነበሩም ሊሆኑም አይችሉም ነበር። ፕሪዚደንት ፑቲን ሲሾሙ እንድርሱ አንገታቸውን ደፍተው የመትፎ አገዛዙን ውስጥ ለውስጥ የሚሸረሽሩ ሀገር ወዳድ ይሆኑ ትናንሽ ፑቲኖች አብረው ተነሱና ፑቲንን ደግፈው አላማቸውን አራመዱ። ፑቲን ብቻቸውን ቢሆኑና የሳቸውን አላማ የሚደግፍ ከሥርዓቱ ውስጥ ባይኖሩ የትም አይደርስም ነበር።

በተዘዋዋሪ በሰሞኑ በአማራ ክልል በተካሄደው ተቃውሞ ሰልፎች ምክንያት አንዳንድ የህወሓት ተንታኒዎች ብአዴን በሰላይዎችና በከሃዲውች የተሞላ ነውና ጽዳት (በሌላ ቃል እስራና ግድያ) ያስፈልገዋል ብለው ይተቻሉ! ውነት ነው ህወሓት ለ26 ዓመት በመግዛቱ በፖሊቲካ ስልጥ ከሌላው ልቋልና እንደዚህ አይነት ነገር ቶሎ ነው የሚገባው። ሌላውም ሊገባው ይገባል።

መጀመርያ የታተመው ከዚህ