Tuesday, 26 June 2018

ስለ ውጭ ሀገር የተወለዱ ያደጉ ልጆች የእናት ቋንቋቸውን አለመቻል ጉዳይ…

በውጭ ሀገር ኑሮ ደጋግመን ያየነው ታሪክ… በአዋቂ እድሜ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በቋንቋቸው እየተነጋገሩ እያሉ አንድ ልጅ ወደነሱ ይመጣል። አዋቂዎቹ ልጁን "Hi, how are you?" ይሉታል ወድያው ንግግራቸውን ወደ እንግሊዘኛ (ጀርመንኛ ወዘተ) ይቀይራሉ! ልጁ አማርኛ፤ ኦሮምኛ፤ ትግርኛ ወይንም ሌላ የኢትዮጵያ ቋንቋ ይችል አይችል አያውቁም ግን ሳያስቡት አይችልም ብለው ገምተው በእንግሊዘኛ ያናግሩታል።

ሁላችንም እንደምናውቀው ውጭ ሀገር የተወለዱ ወይንም በልጅነታቸው ወደ ውጭ ሀገር የሄዱ ልጆቻችን አብዛኞቹ የእናት ቋንቋቸውን አይችሉም። አዎን የተወሰኑ የሚችሉ አሉ ማንበብ መጻፍም የሚችሉ አሉ ግን በርካታው አንዳንድ ቃላት ከመስማት አልፎ አይችልም።

በአንጻሩ በርካታ የሌሎች መጤዎች (ኢሚግራንት) ልጆች የእናት ሀገራቸውን ቋንቋ ይችላሉ። አንዳንዱ ህብረተሰብ የልጅ ልጆቻቸውም ቋንቋቸውን ይችላሉ። ግን አብዛናው ኢትዮጵያዊ ወላጅ ይህንን እውነታ አያውቅም አይገነዘብም። ውጭ የሚኖሩ ልጆች የእናት ቋንቋቸውን አይችሉም ብለን ደምድመናል።

ሆኖም «ለምንድነው ልጆቻችን የእናት ቋንቋቸውን የማይችሉት» ጥያቄ ሁላችንም ደጋግመን እንጠይቃለን። ምዋለ ህጻናት («ዴይኬይር») ስለሚውሉ ነው እንላለን። ትምሕርት ቤት ነው እንላለን። ኑሮ ለማሸነፍ ስለምንሯሯጥ ልጆቻችንን ቋንቋ ለማስተማር ጊዜ ስለሌለን ነው እንላለን። ስንፍነታችን ነው እንላለን። የተለያዩ ምክንያቶች እንሰጣለን።

ግን እነዚህ ምክንያቶች ሁሉን ሌሎች መጤዎችን ይመለከታሉ! ሜክሲካኖች፤ ሌሎች ሂስፓኒኮች፤ ቻይናዎች፤ ህንዶች፤ ጣልያኖች፤ ግሪኮች፤ ሶማሌው፤ አረቦች፤ ቱርኮች ወዘተ ይመለከታቸዋል። እነዚህም ልጆቻቸውን መዋለ ህጻናት እና ትምሕርትቤት  ይልካሉ። እነዚህም እንደኛው ይሰራሉ «ኑሮን ለማሸነፍ» ይጥራሉ ትርፍ ጊዜ የላቸውም። ከነሱ መካከል ሀብታም እና ድሃ አለ። የቀለም ትምሕርት የተማረ ያለተማረ አለ። ከትውልድ ሀገሩ ትንሽ እንግሊዘኛ የተማረ ያልተማረ አለ። አንዳንዱ እንግሊዘኛን እንደ ስልጣኔ የሚቆጥር እና እንደ ጣኦት የሚያመልከው አለ (አንዳንድ ህንዶች) አንዳንዱ ደግሞ ለእንግሊዘኛ ግድ የለውም። ሁሉም አይነት መጤዎች አሉ። ግን እነዚህ በሙሉ ከኛ ኢትዮጵያዊያን በተሻለ መልኩ የእናት ቋንቋቸውን ለጆቻቸው ያስተላልፋሉ።

ታድያ ለምንድነው የኢትዮጵያዊ ልጆች ከነዚህ ሁሉ ተለይተው የእናት ቋንቋቸውን የማይችሉት? መልሱ የሚመስለኝ እንዲህ ነው፤ የልጆቻችን የእናት ቋንቋቸውን አለማወቅ ሳናውቀው ባህል ሆኗል። የመጀመርያ ኢትዮጵያዊ መጤዎች በተለያዩ ምክንያቶች ልጆቻቸውን ቋንቋ ሳያስተምሩ ቀርተው የውጭ ሀገር ልጅ የእናት ቋንቋ አለማወቅ በህብረተሰባችን የተለመደ ሆነ። ይህ "expectation" ባህል ሆነብን።

ምክነያቱ ከዚህ የሚያልፍ አይመስለኝም። ከላይ እንደጠቀስኩት ከሌሎች መጤዎች ምንም አንለይም። ስለዚህ የባህል ጉዳይ ነው። የአቅም ማጣት ወዘተ አይደለም። ይህን ባህል ከቀየርን እና ልጆቻችን እንደ ማንም ልጆች የእናት ቋንቋቸውን ሊያውቁ ይችላሉ ብልን ከደመደምን አንድ ትልቅ እርምጃ ወሰድን ማለት ነው።

ሁለተኛው እርምጃ ልጆቻችንን በቋንቋችን ብቻ ማናገር ነው። ከተወለዱ ጀምሮ ወላጅ እና ልጅ በማንኛውም ቦታ በቋንቋቸው ብቻ ነው የሚነጋገሩት የሚል ህግ ማውጣት ነው። ቀላል ነው። የተለየ ነገር አያስፈልግም። ቋንቋውን ቅጭ ብሎ ማስተማር አያስፈልግም። ከወላጅ ምንም ትርፍ ስራ አይጠይቅም። ልጆችን በቋንቋ ማነጋገር ብቻ ነው። ሌሎች ሁሉ እንደዚሁ ነው የሚያረጉት። እርግጥ መጻፍ እና ማንበብ መማር ትምሕርት ይጠይቃል ግን በልጅነት ከተጀመረ ትንሽ ጊዜ ነው የሚጠይቀው። ልጆች በትንሽ እድሜ በቀላሉ ፊደሉን መማር ስለሚችሉ ከዛ በኋላ እራሳቸው ይቀጥሉበታል።

በዚህ መልኩ ልጆአቸውን ቋንቋቸውን ያስተማሩ ሰዎች ሁላችንም እናውቃለን። ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም መጻፍ ማንበብ የሚችሉ አሉ። ግእዝም የሚችል አውቃለሁ! እንደሚቻል መረጃ አለን ትርፍ ስራ እና ጊዜ እንዳማይፈጅም መረጃ አለን። ስለዚህ እንበርታበት!

በመጨረሻ አንድ ነገር ልጨምር እወዳለሁ። የእናት ቋንቋን መቻል ጥቅሙ ምንድነው ብላቸሁ የምትጠይቁ ትኖራላችሁ። ጥሩ ጥያቄ ነው። ልጄን አሜሪካ ወልጄ የማሳድግ ከሆነ አማርኛ መቻሉ ምን ዋጋ አለው? ስፓኒሽ አይሻለው ይሆን? መቼም የእናት ቋንቋችንን ማውቅ አስፈላጊነቱን ሁላችንም ምክንያቱን መደርደር ባንችልም ከልባችን እናውቀዋለን። ግን ምክንያቶቹን እስቲ ልደርድር፤

1. ማንነት፤ ውጭ ሀገር የተውለደ ኢትዮጵያዊ ቢፈልግም ባይፈልግም እራሱን እንደ ሙሉ የውጭ ሀገር ዜጋ ሊቆጥር አይችልም። በሰው ልጅ ተፈጥሮ ምክንያት የአባቶቹ ማንነት ይጫነዋል ከዬት ናቸው ማን ናቸው ማለቱ አይቀርም። ሁላችንም ይህንን በተግባር አይተናል ልንክደው አንችልም። ቋንቋን ማወቅ ይህን የማንነት ስሜትን በተወሰነ ደረጃ ያሟላል።

2. ኢትዮጵያዊ ነን ሀገራችንን እንወዳለን እዚህ ስደተኛ ነን ብለን የምናምን ልጆቻችንን ኢትዮጵያዊ ማድረግ አለብን አይደለ? አይ ልጆቻችንን አሜሪካዊ፤ ጀርማን ወዘተ እናድርግ ይህዱ ከሆነ ጥሩ ግን ምን እያደረግን እንደሆነ እንወቀው። ዜጋን አልፎ መስጠት እንደ ትንሽ ነገር አኑቅጠረው። መብት ቢሆንም ለኢትዮጵያ ኪሳራ ነው።

3. በተዘዋዋሪ በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የራስን ማንነት ማወቅ ለሌላ የኑሮ መስፈርት ይረዳል። ለትምሕርት፤ ከሰው ጋር ለመግባባት፤ ቁም ነገረኛ ለመሆን ወዘተ የራሱን ማንነት እና ከየት የመጣ እንደሆነ የሚያውቅ ልጅ በሁሉም ይሻላል።

ስለዚህ ልጆቻችንን የእናት ሀገር ቋንቋቸውን እናስተምር ወይም ብትክክሉ ለመናገር አንከልክል! በቋንቋቸው እናናግራቸው እና ወደ ፊት ማንነታቸውን የሚያውቁ የሚኮሩ ልጆች እንዲሆኑ እናድርግ።

-------------------------

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!