ይህንን ታሪክ ደጋግመን አይተነዋል ብቻ ሳይሆን አሳልፈነዋል። የጎሳ ፖለቲካ በአገራችን ጎልቶ መታየት ከጀመረ ወዲህ፤ ከነጀብሃ፤ ሻብያ፤ ህወሓትና ደርግ ዘመን ጀምሮ የተደጋገመ ታሪክ ነው። በነጻነት ወይም ፍትህ ወይም «መብት» ጥያቄ ይኖራል። የሚጣሉት ጎራዎች በጥያቄው ላይ ከማተኮር ጉዳዩን ወደ ጎሳን ወይም ዘርን ያዞሩታል። ለጎሳ ጥል ምክንያት ይጠቀሙበትና የነጻነት ወይም ፍትህ ወይም መብት ጥያቄው ቀርቶ የጎሳ ውግያ ይሆናል። ጎሰኝነትን እንደ መሳርያ ይጠቀሙበታል አገርን ያጠፉበታል። (ይህን ስል በመጀመሪያ የተነሱት ጥያቄዎች መሰረተ ቢስ ነበሩ ማለቴ አይደለም ወይም በጎሳ ወይም ቋንቋ ዙርያ ችግር አልበረም አልልም። ሆኖም ጎሳ እንደ መሳርያ መጠቀም አላስፈላጊና ጎጂ ነበር፤ አሁንም ነው።)
ዛሬ በኢትዮጵያዊያን ብዙሃን በትግራይ ቅሬታ መኖሩ የማይካድ ነገር ነው። ዲያስፖራ የሚኖር ካልሆነ የትም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ይህን ሃቅ በየቀኑ የሚያየውና የሚኖረው ነው። ይህ በትግሬዎች ላይ ያለው ቅሬታ ደግሞ በተቃዋሚ ወይም «ፀረ ሰላም ሃይሎች» የተቀሰቀሰ አይደለም። (ተቀዋሚዎች ምንም ለመቀስቀስ አቅሙም ትብብሩም የላቸውምና።) ከሊስትሮው እስከ ሃብታም ነጋዴው እስከ የቤት እመቤቷ እስከ ካህኑ እስከ ተማሪው ይህንን የቅሬታ ስሜት አለው። ያሳዝናል ግን ያለ ነገር ነው። የጎሳ ጉዳይ ሳይሆን የፖለቲካ ጉዳይ ነው መሆን የነበረበት፤ ሰውዉ ስለትግሬ ሲአማርር «ተውዉ፤ ገዥ መንግስቱ ሌላ ፖለቲካ ስለማይፈቅድ ብቸኛ ስልጣን ስለያዘ ነው ግፍ የበዛው» ብዬ ለማስረዳት ብሞክር ማንም አይሰማም። ሰውዉ በትግሬ በላይነት አምኖ ሌላ ነገር አይሰማም።
መንግስትንም ያስጨነቀው ይህ ነው። ከመሪ ወይም ተቃዋሚ መደብ ሳይሆን የብዙሃኑ የህዝቡ ብሶት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው መንግስት ለውጥ ለህልውናው ግድ እንደሆነ አምኖ እርስ በርሱ የሚወያየው።
በዚህ ሁኔታ ትግሬዎች አለ አግባብ ተጥቅተዋል ገና ሊጠቁም ይችላሉ። ጥያቄ የለውም። (እዚህ መጥቀስ የምፈልገው ግን እድሜ ለብዙሃኑ ታሪካዊ ዝንባሌ ጎሰኝነት እንደ የ27 ዓመታት የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ያህል አያጠቃውም። ሆኖም ያለውም መጠን ችግር ነው።) ግን ይህ ፍግ መቆም አለበት፤ ትግሬ መጠቃት የለበትም ብሎ መጮህ ምን ዋጋ አለው? ማን ይሰማናል? ከላይ እንደጠቀስኩት ህዝቡ ትግሬዎች አንደኛ ዜጋ ናቸው ሌሎቻችን ሁለተኛ ዜጋ ነን ብሎ ደምድሟል። አይደለም የፖለቲካ ጉዳይ ነው፤ አማራ ክልል ጭቋኙ አማራ ነው ኦሮሚያ ጮቋኙ ኦሮሞ ነው ብንል አልሰሙንም አሁንም አይሰሙንም።
ስለዚህ መፍትሄው ከተቃዋሚ ወይም «ኢሳት» ወዘተ እጅ አይደለም። መፍትሄው ከመንግስት ብቻ ነው መምጣት የሚችለው። መንግስት ዙሪያ ያለነው በሙሉ ሃይላችን መንግስት የሚያስፈልገውን ለውጦች እንዲያመጣ መግፋት አለብን። በተለይ ለተጋሩ መጠቃት ዋናው መፍትሄ የመንግስት የጎሰኝነት አቋምና ፕሮፓጋንዳውን መቀየር ነው። በህዝቡ ልብ የ26 ዓመታት የጎሳ ስሜት በመሸርሸር ነው ያሉትን ቅሬቴዎች ከጎሳ ወደ ፖለቲካ መቀየር የሚቻለው።
አንድ ነገር መርሳት የለብንም። ይህንን ትጠንቅቃችሁ እንድታነቡ ብትህትና እጠይቃለሁ። የኢህአዴግ አቋም፤ በእርግጥ አብዛኛው የተማሪዎች የፖለቲካ ንቅናቄ አቋም፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሃበራዊና ኤኮኖሚ ቅሬታዎችና ችግሮች በጎሳ የተመሰረቱ ናቸው ነው። ይህ ነው የኢህአዴግ አቋም። ጭቆና አለ? የጎሳ ችግር ነው። እኩልነት የለም? የጎሳ ችግር ነው፡ ድህነት አለ? የጎሳ ችግር ነው። የጎሳውን ችግር ከፈታን ሁሉም ይፈታል። ታድያ ዛሬ ህዝቡ ችግራችን በሙሉ በትግሬ የበላይነት ምክንያት ነው ካለ በትክክል የኢህአዴግን አቋም ነው የሚያንጸባርቀው ማለት አይደለምን?! የጎሳ ፖለቲካ እንዴት አደገኛ እንደሆነው አያችሁ። ትግሬዎች ደግሞ መልሳቸው የምንጠቃው በኢህአዴግ ብቸኛ ስልጣን በመያዝ ሳይሆን በትሬነታችን ነው ብለው ይመልሳሉ። ምን ይደረግ፤ ችግሩን ወደ ጎሳ በማውረድ አብሮ ገደል መግባት ነው።
ስለዚህ ብእራችንንና ድምጻችንን አቅመ ቢስ የሆኑት ትቃዋሚና «አክቲቪስት» ላይ ከማባክን መንግስት አቋሙን እንዲቀይር ብለን እናሳምነው። መንግስት የሃሳብ እርዳታ ያስፈልገዋል። የ40 ዓመት ጣኦት የሆነ ርዕዮተ ዓለሙን መቀየር እጅግ ከባድ ነውና መንገዱም በጥንቃቄ የተአሰበበትና የታቀደ መሆን አለበት።
በትግሬ በትግሬነቱ የሚደርስበት ጭቆና ይውደም! የሚያወድመው ግን የኢህአዴግ የውስጥ ለውጥ ነው።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!