Saturday, 27 January 2018

እንሆ ፑቲኖቻችን!

አንድ አመት ተኩል ይሆናል ርእሱ «ፑቲኖቻችን የት አሉ» የሆነውን ጽሁፍ ከጻፍኩኝ። እንሆ በነ ለማ መገርሳ፤ አቢይ አህመድና ሌሎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህንን የፑቲን ሚና ሲጫወቱ እናያለን። እንኳን ለዚህ አደረሰን!

ለማስታወስ ያህል የ«ፑቲን» ብዬ የሰየምኩት የፖለቲካ ሚና ባለው የፖለቲካ ሥርአት ውስጥ ሆኖ ውስጥ ለውስጥ በስውር ራሰን አለጊዜው ሳያጋልጥ ለውጥ ማምጣት ነው። የሩሲያው ቭዲሚር ፑቲንን ታሪክ ለማስታወስ ያህል አቋሙን በሚጠላው የድሮ አለቃው ቦሪስ ዬልትሲን መንግስት ይሰራ ነበር። አቋሙን በሞላ ጎደል ደብቆ እራሱንም የሱ አይነት አቋም ያላቸውን ባልደረቦቹንም ሰውሮ ውስጥ ለውስጥ ተደራጀና የአለቃው ዋና አጋዥ ሆነ። ዬልትሲን ከስልጣን ሲወርድ ጭራሽ ፑቲንን ሾመና እንደሚባለው «ሌላው ታሪክ ነው» ፑቲን የሩሲያን የፖለቲካ ሁኔታ በትክክሉ ገምቶት ነበር፤ እራሱን ከሥረዓቱ ውጭ አድርጎ ምንም አይነት ለውጥ ሊያመጣ እንዳማይችል ገብቶቶ በበር። ይገደል ነበር ወይም ከሀገር ይባረር ነበር። ሌሎችም የሱ አጋሮች ይህንን ተገንዝበው ውስጥ ሆነን በትዕግስት እራሳችንንም ንቅናቄያችንን አደራጅተን ጊዜው ሲደርስ በልጠን እንገኛለን ብለው ወሰኑ። እንዳሰቡት ሆነ።

እነ ለማ መገርሳም እንደዚህ ነው ያደረጉት። ጊዜው ሳይደርስ አጉል የፖለቲካ እርምጃ በመውሰድ ከጨዋታው ከሚፈነገሉ ቀስ ብለው አንገታቸውን ደፍተው ድራቸውንም የፖለቲካ ኃይላቸውንም አጎልብተው አሁን ትልቅ ሚና መጫወት የሚችሉበት ደረጃ ደረሱ። (ሌሎቻችን አክሩፈን ከስርአቱ ውጭ ሆነን ምንም ሳናደርግ እነሱንም ሳንረዳ።)

አሁንም ግን እነ ለማ እጅግ ከባድ መንገድ ነው የሚጠብቃቸው። መአት ተቃዋሚና ጠላቶች አሏቸው ከኢህአዴግ ውስጥ ከህወሓት ውስጥ ከኦህዴድም ውስጥ። ደጋፊዎቻቸውን ማብዛት ተቃናቃኞቻቸውን ማድከም ከባድ ስራ ነው የሚሆነው። ይበልጥ ደግሞ ዝም ያለውንና መሪ ቢስ የሆነውን ብዙሃኑን ማደራጀትና ወደ አንድ አቅጣጫ መምራት እጅግ ከባድ ስራ ነው። እግዚአብሔር ይርዳቸው፤ በነሱ ቦታ መሆን በፍጹም አልመኝም።

እዚህ ላይ ሁላችንም የኢትዮጵያ አንድነት፤ የአገር ብሄተኝነት ወዳጆች ችግራቸውንም አቅማቸውንም በትክክል እንድንረዳ ይገባል። በተፈጠረው ጉዳይ በሙሉ ዘራፍ ብለው አደገኛና ብልህ ያልሆን እርምጃ እንዲወስዱ አንጠብቅ። ያላቸውን የሃይልና የድጋፍ መጠን ያውቁታል። ጉዛዋአቸው ረዥም ነው፤ ማራቶን ነው እንጂ መቶ ሜተር ሩጫ አይደለም።

ለምሳሌ ያህል ወልዲያ በተፈጸመው ኢሰባዊ ድርጊት ተነስተው እነ ገዱ አንዳርጋቸው ይጩሁ ማለት ጥሩ ጥያቄ ቢሆንም ባይጮሁ ወይም እንደምንፈልገው ባይናገሩ አንበሳጭ። ትእግስት፤ ትእግስት። ከአንደኛ ወደ አራተኛ ማርሽ መሄድ አደገኛ ነው። እነዚህ ሰዎች በፓርቲዎቻቸው ያላቸውን ተሰሚነትና ኃይል ቀስ ብለው ያደራጁ። ከፍ ባሉ ቁጥር ይበልት ደፋር የሆነ እርምጃ መውሰድ ይችላሉ። ግን ደረጃውን አንድ በአንድ መውጣት አለባቸው። ልክ ፑቲን እንዳደረገው።

በመጭረሻ ላስታውሳችሁ የምወደው እነ ለማና ሌሎች በስልጣን ላይ ስለሆኑ የሚታዩ ቢሆንም ከነሱ በታች ብዙ የነሱን አቋም የሚጋሩ አሉ። አለነሱ ብቻቸውን ሊሰሩ አይችሉም ነበር። እነሱም እንደ እባብ ብለህ መሆን አለባቸው። ሌሎቻችንም ከኢህአዴግ ውጭ ያለነው እራሳችንን ገምግመን ውስጥ ገብተን ብንረዳቸው ይመረጣል።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!