Wednesday, 31 January 2018

ዳግም ጥሪ ለኢትዮጵያዊ ምሁራን

ውነቱን ለመናገር ጥሪው ለምሁራን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አቅም ላለው መሆን አለበት። መልካም ለውጥ ለኢትዮጵያ የሚመጣው ከነ ለማ መገርሳ፤ አቢይ አህመድና ገዱ አንዳርጋቸው አይነቱ ጋር አብሮ በመስራት ነው። እነዚህ ማድረግ የቻሉት ዋናና የተለየ ነገር ካለው መዋቀር ውስጥ ሆነው እንደ እባብም እንደ እርግብም ሆነው መስራትና መታገል ነው። አሁን ደግሞ የኛ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ጭብጨባና አጉል ሙገሳ ሳይሆን እርዳታ ነው እጅግ አንገብጋቢ ሆኖ የሚያስፈልጋቸው። የኢህአዴግን መርከብ ወደነሱ አቋም ለመምራት በርካታ አብረዋቸው የሚሰራ የሰው ሃይል ("critical mass") ያስፈልጋቸዋል። እርግጥ ኢህአዴግ ውስጥ ሌሎች የነሱ አይነት የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ይኖራሉ። ነገር ግን ቁጥራቸው ለውጥ ለማምጣት በቂ አይደለም። ተጨማሪ የሰው፤ የሃሳብ፤ የሃይልና የአቅም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

ስለዚህ ፖለቲካ ውስጥ አልገባም፤ ኢህአዴግ ውስጥ አልገባም፤ ሀገር ውስጥ አልኖርም ወዘተ የምንለው በአስቸቋይ ስሜታዊነታችንን አሸንፈን ወደ ሀገር ወደ ፖለቲካ መዋቅር በተለያየ መስፈርት መጠጋት አለብን። «አደገኛ ነው» «ዋጋ የለውም» «አይሰራም» ትሉኛላችሁ? ብላችኋልም ለዓመታት። ግን እድሜ ለእነ ለማ መገርሳ ይህ አስተያየት ውድቅ እንደሆነ ተረጋግጧል። ብልህ ከሆንን፤ ጸንፈኛ ካልሆንን፤ ትህትና ካለን፤ የሃሳብ መቀየር አቅም ካለን፤ አብሮ መስራት ከቻልን ይቻላልም ይሳካል። ለችግራችንም መፍትሄ ይሆናል።

ይቻላል ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ብቸኛ መንገዱ ይህ ከውስጥ መስራት ነው። ከመዋቅሩ ውጭ ወይም ይባስ ከሃገር ውጭ ሆኖ ደህና ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል የርዥም ዓመታት መረጃ አለን። «ተቃዋሚ» የምንባለው ባለፉት 40 ዓመታት ታሪክ ምክንያት እጅግ እንደደከምንና አቅም እንዳጣን ይታወሳል። ስለዚህ ያንኑ የማይሰራ ዘዴ ከመሞከር፤ ጭንቅላታችንን ደጋግመን ከድንጋይ ግድግዳ ጋር ከማጋጨት ሌላ ደህና የመሳካት እድል ያለውን መንገድን መሞከር ተገቢ ነው። ይህ ደግሞ ካለው መዋቀር ውስጥ በዘዴ እንደነ ለማ መገርሳ መስራት ነው

ስለዚህ አቅም ያላችሁ ተሳተፉ። አትፍሩ። እራሳችሁን ሳታጋልጡ በአቅማችሁ ስርስራችሁ ግቡ። ካቃታችሁ ሽኩም ይበዛብኛል ካላችሁ ይሁን፤ ይህ ስራ ለሁሉም የሚሆን ያደለም። ግን ቢያንስ አይቻልም አትበሉ። እኔ አልችልም እንጂ ይቻላል በሉ። ተስፋ ቆራጭ አትሁኑ። እነ ለማ የጀመሩትን እናንተም መከተል ትችላላችሁ!

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!