Sunday, 4 December 2016

መደጋገም አለመሻሻል

እንደጠበኩት የ2008-2009 የህዝብ ዐመፅ ተረጋግቷል። የተረጋጋው መንግስት የአስሸኳይ አዋጅ ስላወጀ፤ የማይሸነፍ ኃይልና አቅም ስላለው፤ ህዝቡ አቅም ስለሌለው፤ ህዝቡ ስለተከፋፈለ፤ አብዛኛው ህዝብ ኢህአዴግን ስለሚደግፍ፤ ወዘተ አይደለም። ዐመፁ የመነመነው ህዝቡ በተለይም የፖለቲካ መደቡ የኢትዮጵያ የመንገስት አገዛዝን ለመቀየር የሚያስፈልጉ ቀድመ ዝግጅቶች ስላላሟሉ ነው።

እነዚህ ቀድመ ዝግጅቶች ምንድናቸው? አንድ አገዛዝን ለመቀየር በመጀመርያ አማራጭ መቅረብ አለበት። አማራች የፖለቲካ ራዕይ ወይም ሰፊ አመለካከት፤ ርዕዮት ዓለም፤ መዋቅርና ኃይል ያስፈለጋል። ከዛ በኋላ ነው ህዝቡ በሰላም ወይም በዐመፅ፤ በቀስታ ወይም (ቢቀርብን ይሻላልንጂ) በአብዮት፤ ካሉት የመንግስት አስተዳደር አማራቾች የሚመርጠው።

ላለፉት 25 ዓመታት ግን የኢህአዴግ ተቃዋሚዎች፤ ማለት ህዝብም የፖለቲካ መደቡም፤ እነደዚህ አይነት የፖለቲካ አማራጭ ማዘጋጀት አልቻለም። በመጀመርያ የፖለቲካ አመለካከቱም ርዕዮት ዓለሙም የተበታተነና ያልሰከነ ነው። የተለያዩ አመለካከቶች አሉ ከጎሰኝነት እስከ አንድነትና ሌሎች ከመካከል። ይህ ልዩነቶች ተገቢ ቢሆንም እነዚህ አመለካከቶች እንደሆነው ሆኖ ለመስማማት ተስማምተው አብሮ መስራት አልቻሉም። ይባስ ተመሳሳይ የፖለቲካ አስተያየት ያላቸው እርስ በርስ በተራ ምክነያቶች እየተጣሉ አይስማሙም። በኦሮሞ ብሄርተኞች መካከል ወይም በኢትዮጵያ ብሄርቶኞች ወይም የአንድነት ፖለቲካ ደጋፊዎች መካከል ያለው አለመስማማትና አብሮ አለመስራት ነው ዋናው ችግር። ለመድገም ያህል በጎሳና በአንድነት አመለካከት ያለው አለመስማማት አደለም ትሉቁ ችግራችን። ዋናው ችግራችን አንድ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ትስማምተው መስራት አለመቻላችን ነው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር በአንድ አረፍተ ነገር ለመቋጨት ከተፈለገ ይህ ነው። በዚህ ምክነያት የኢህአዴግ ተቃዋሚ አንድ የሆነ ወይም ሁሉን አቀፍ የሆነ የፖለቲካ አማራጭ አመለካከትና ርዕዮት ዓለም ለ25 ዓመት መገንባት አልቻለም።

አንድ የአማራጭ አመለካከት ከሌለ ደግሞ መዋቅር ሊኖር አይችልምና ለዚህም እስከ ዛሬ አማራጭ መዋቅር የለም። ሻእቢያና ህወሃት በደርግ ጊዜ የነበራቸውን መዋቀር እናስታውስ። የዘመኑ ተቃዋሚ እነደዚህ አይነት ነገር በኢትዮጵያ ውስጥም ውጭም የለውም። እነ ሻእቢያ በጄታቸው በሚሊዮን ብር ሲቆጠር የዛሬ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች በሺዎች ይቆጠራሉ! እንደዚህ አይነት መዋቅሮች ምን ብለው ነው መንግስት የሚወርሱት?

መዋቅር ስለሌለ ደግሞ ኃይል የለም። የተቃዋሚ የህዝቡም ኃይል በሺዎች ነው የሚቆጠረው። በፊሊፒንስ ሀገር የህዝብ አብዮት ሲነሳ ህዝቡ በሚሊኦን ነበር ወደ ሰልፍ የወጣው። አንድ ጥይት ሳይተኮስ  መንግስት በሰላም ተቀየረ። ኢትዮጵያ ግን ውስን ቁጥር ነው ሰልፍ የሚወጣው። የተቃዋሚ የጦርም ኃይል ኢሚንት ነው። ረብሻ ለመፍጠር ያህል አቅም ቢኖራቸው ነውንጂ በዚህ ሁኔታ ከዛ አልፎ የተም አይደርስም።

እሺ፤ የፖለቲካ አመለካከት ወይም ርዕዮት ዓለም የለም። መዋቅርም የለም። ኃይልም የለም። ታድያ ምንድነው የሚጠበቀው? ከ25 ዓመታት በኋላ ተቃዋሚው ጎራ በሞላ ጎደል ምንም መሻሻል አላሳይምም የበፊቱንም ስህተቶች ደጋግሞ ይደጋግማል።

የዛሬውን የምሁራንና የተቃዋሚ መሪዎች ውይይት ሲታይ ከ25 ዓመት በፊት ከነበረው ብዙ ለውጥ የለውም። ምናልባትም ወደ ኋላ ሄደናል። 25 ዓመት በፊት የታተመ ኢትዮጵያን ሪቭዩ መጽየትን ብንመለከት ያው ዛሬም የምንወያይበት ጉዳዮች ያኔም (ያኔ በተሻለ ቋንቋና ብስለት) እየተወያየን ነበር። በውይዩቱ ውይም በመግባባቱ ምንም ለውጥ አይታይም!

ገጣሚው አቶ ፍቅሬ ቶሎሳ 25 ዓመት በፊት በገጣሚ አቅሙ ስለኦሮሞና አማራ ግንኙነት የሚገጥሙትን ዛሬም ይጽፋሉ ያኔም ዛሬም በቂ የተረዳቸው ስለሌለ። አንድ ኦሮሞ ብሄርተኛ ኢትዮጵያ መገነጣጠል አለባት ሲሉ ጉዳዩን እንደተለመደ አድርጎ በበሰለና በሰከነ መንገድ ተመልክቶ የሚገባውን መልስ ከመስጠት ልክ እንደ 25 ዓመት በፊት በድንጋጤ - ይህ ያላሰብነው የጎሳ ብሄርተኝነት እውነት ሊመጣብን ነው እንጂ እያልን - የተበታተነና መላ የሌለው መልስ መለስን ፍረሃትንም አንጸባረቅን። ትናንሽ የስራ አለመግባባት ሲያጋጥማቸው «የአማራ ንቅናቄ ደጋፊዎች» በፖለቲካ አመለካከት የሚጋሩትን ግንቦት 7 ደግሞም ኢሳትን መሳደብ ጀመሩ ልክንደ 25 ዓመት የአንድነት ደጋፊዎች ከላይ የጠቀስኩትን ታላቅ ኢትዮጵያን ሪቪዩ መጽየት ተጣልተው እንዳፈረሱት። ለማስታውስ ያህል ከዛም በኋላ መላው ኢትዮጵያ ወይም መላው አማራ ትብሎ ኃይለኛ ፍጅት ተቅሄደ። ቀጥሎ የቅንጅት ፍጅቶች፤ የአንድነት ፓርቲ ፍጅት፤ ዛሬም የሰማያዊ ፓርቲ ፍጅት! እንሆ ከ25 ዓመት በኋላ ታሪክ እየተደገመ ነው!

መፍትሄው ምንድነው? በዋና ጉዳዩ ላይ ስራ መስራት ነው። የሰው ልጅ ችግር እንዳለውና ማስተካከል ካልፈለገ ለመሸሽ ያህል ሌሎች ላይ ወይም በሌላ ጉዳይ ያተኩራል። ዋናው ችግሩ እንዳለ ወይም እየባሰ ይቀጥላልም። እስካሁን የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ጎራ  እንደዚህ ነን። በዋናው ጉዳይ ስራ ከመስራት መጣላትና መናቆር ላይ ቆይተናል። ግን ወደ ግብ የምሄድ ፍላጎት ካለን እነዛን አሳሳች ተግባሮችን ትተን ወደ ስራ መግባት አለብን።

እነዚህ ስራዎች ምንድናቸው? የፖለቲካ አመለካከትን ተወያይቶ ቀስ ብሎ ጨምቆ ሰፊ ግን አንድ የሆነ የአገዛዝ አመለካከት አዘጋጅቶ በዚ ላይ መስማማት። ይህ ስምምነት መዋቅር ለመዘርጋት ዋና ቀድመ ዝግጅት ነው። መተዋወቅ፤ መግባባት፤ መስማማትና አንድ ልብ መሆን ግድ ናቸው። ይህ ደግሞ ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሂደት ነው። በቅርቡ ባደረጉት ቃለ ምልልስ አቶ ጁኔዲ ሳዶ በአንድ ወቅት ኦኸድድ የ20 የሙሉ ቀን ውይይት ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ጋር እንዳካሄደ ተናግረዋል። ይህ ረጅም ውይይት በተዋቀረ ድርጅት ውስጥ ነበርና አዲስ ድርጅት ወይም ስብስብ ምን ያህል ውይይት እንደሚያስፈልገው እናስብ።

አንድ ሰፊ ግን አስማሚ አመለካከት ላይ ከተደረሰ በኋላ መዋቅር መዘርጋት ነው የሚቀጥለው እርምጃ። ይህ በተነጻጻሪ ቀላሉ እርምጃ ነው የሚሆነው። አንድ ልብ የሆነ ሰው እጅግ ስኬታማ ይሆናልና። ይህ መዋቅር አንድ ድርጅት ብቻ ሊሆን አይገባም። የተለያዩ መዋቅሮች - የታወቁም የህቡ - በተለያዩ የህብረተሰብ ዘርፍ ይቋቋማሉ። በርካታ ሰዎችም ዛሬ ባሉት የሀገሪቱ መዋቅሮች ከነ ኢህአዴግ ውስጥ ሰተት ብሎው ገብተው የራሳቸውን የሚያምኑበትን አቋም በድብቅ ያራምዳሉ።

ይህ መደራጀት እይጠነከረ ሲቀጥል በራሱ ትልቅ ኃይል ዪሆናል። በዚህ ወቅት የጠመንጃ ኃይል አያስፈልግም! እያንዳኑ የሀገሪቷ ዘርፍ በነዚህ የተቃዋሚው ጎራ ሰዎች ሞልቶ ይገኛልና ትንሿ እንቅስቃሴ አገዛዙን በሰላም ግልብጥ ያረገዋል። የነባር መንግስቱ ተራም ቀንደኛም ባለስልጣኖች በግድ ቢሆንም በተቃዋሚው ብስለት ምክንያት አለ ፍርሃት ለውጡን ይቀበላሉ።

በኔ እምነት የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሻሻል ቀደም ተከተል እንዲህ ነው መሆን ያለበት። የተሻለ ምርጫ የለም። ግን ከ25 ዓመት በኋላ አሁንም በተወሰነ ደረጃ ገና አንደኛ እርምጃው ላይ ነን። ስራችንን እንጀምር።

No comments:

Post a Comment

ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!