የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን በሀገራችን ፖለቲካ ምን አይነት ሚና መጫወት አለብን የሚለው ጥያቄ ሰፊና ውስብስብ ነው። ከዚህ ጽሁፍ በዚህ ጉዳይ ላይ አንዳንድ መሰረታዊ የሚመስሉኝን ሃሳቦችን ማቅረብ እወዳለሁ።
1. በእምነታችን እግዚአብሔር ከሁሉም ቦታ በሁሉም ጊዜ በሁሉም ዘመን ይገኛል። እግዚአብሔር የሌለበት ስፍራ የለም። ይህ ማለት ዓለምን በተለምዶ «ዓለማዊ» እና «መንፈሳዊ» ብሎ መለየት አይቻልም። እግዚአብሔር በቤተሰባችን፤ በመስሪያቤታችን፤ በንግዶቻችን፤ በትምሕርትቤቶቻችን፤ በእስርቤቶቻችን፤ በፖለቲካችን፤ በሁሉም ቦታ አለ። ስለዚህ ለእምነታችን off limits የሆነ ቦታ የለም። ሊኖርም አይችልም። ግን ጥያቄው እንዴት ነው እምነታችንን የምናንጸባርቀው ነው! እውነት እምነታችንን እናንጸባርቃለን ወይንም ኑፋቄ፤ ሰላም እናንጸባርቃለን ወይንም አመጽ፤ ደግነት እናንጸባርቃለን ወይንም ክፋት?
2. ክርስቶስ ፍቅርና ሰላም ነውና የክርስትና በፖለቲካ ላይ ያለው አመለካከት ፍቅርና ሰላም መሆን አለበት። መፈለግ ያለብን ሰላምን የሚያሰፍን እና ፍኩ ነገር የማያስደርገን (do no harm) ፖለቲካ ነው። ሁሉ አካሄዳችን በነዚህ ሁለት መርህዎች ስር መሆን አለበት። ሁሉ አቋሞቻችን በነዚህ መርህዎች መፈተሽ አለባቸው። ይህን ወይንም ያንን ፖሊሲ ወይም ፖለቲካዊ ተግባር ይጽደቅ ወይንም ይፈጸም ስንል ይህ ፖሊሲ ወይንም ተግባር ሰላም ያመጣል ወይ እና ክፉ እንዳናደርግ ይከለክለናል ወይ ብለን መጠየቅ አለብን።
3. በሃይማኖታችን አንድ እውነት አለ፤ ይህ እውነት የኦርቶዶክሳዊ እምነታችን ነው። በዚህ በሃይማኖታችን መደራደር አይቻልም። ግን ከሃይማኖት ውች ሁሉ ነገር አሻሚ ነው። የፖለቲካ አቋም፤ ፖሊሲ፤ አተገባበር ሁሉ ትክክል ሊሆን፤ ሊሳሳት፤ መስተካከል ሊኖረው ይችላል። ፍፁም እውነት የሆነ ፖለቲካ የለም። ፖለቲካ እንደ ማንኛውም ስራ ግብአሩን እና ውጤቱን መርምሮ ገምቶ የሚሰራ ነው። ስተት ሊኖር ይችላል፤ ስተት ይኖራል። ግምቶችም ግቦችም የተሳሳቱ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ክርስቲያኖች የፖለቲካ አቋምን እንደ ጣኦት እንዳንቆጥር በጣም መጠንቀቅ አለብን። «ሶሽያሊዝም»፤ «ዴሞክራሲ»፤ «ሚክስድ ኤኮኖምይ»፤ «ነጻ ገበያ»፤ «ንጹህ ኤነርጂ» ወዘተ ሁሉም ሊጠቅሙ ላይጠቅሙ ይችላሉ። ከእሴቶቻችን ጋር አወራርድን የሚሆነውን ወስደን የማይሆነውን ትተን መራመድ ነው። እንደ ሁኔታው፤ ጊዜው፤ እና ችግሩ አቋምና ተግባራችንን ማስተካከል። የተለየ አቋም ያለውን አለመውቀስ ልንሳሳትንችላለንና። ፖለቲካ ጣኦት አይደለም!
4. ትህትና (humility) አንዱ የሃይማኖታችን ዋና እሴት ነው። «የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።» የሃይማኖት አባቶቻችን ከድርሳናቶቻቸው ትህትና ላይ በጣም ያተኩራሉ። ክርስቲያን በማንኛውም ስፍራ ትህትናውን መጠበቅ አለበት በፖለቲካ ስፍራውም እንዲሁ። የፖለቲካ አቋም ስንወስድ ተሳስተን ይሆናል ብለን ማሰብ አለብን። ከላይ እንዳልኩት ፖለቲካ ጣኦት አይደለምና አቋሞቻችንን እንደ ፍፁም አርገን መውሰድ አንችልም። ትህትና የግድ ነው። የትህትና ተቃራኒ እብሪት ክፉ ነው።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!