የታወቀው የመካከለኛ ምስራቅ ታሪክ ምሁር በርናርድ ልዊስ የአረብ ፖለቲካ ባህል ድክመትን ለመተቸት እንዲህ ብሎ ነበር፤
“When people realize things are going wrong, there are two questions they can ask......One is, ‘What did we do wrong?’ and the other is, ‘Who did this to us?’ The latter leads to conspiracy theories and paranoia. The first question leads to another line of thinking: ‘How do we put it right?’”
ትርጉም፤ «ህዝብ ነገሮች እየተበላሹ እንደሆነ ሲገነዘብ ሁለት አይነት ጥያቄዎችን መጠየቅ ይችላሉ፤ አንዱ «ምን ተሳስተን ነው?» ነው፤ ሌላው ጥያቄ «ማን ነው እንደዚህ ያደረገን ነው?» የመጨረሻው አይነት ጥያቄ ወደ ሴራ፤ ፍረሃትና ጥርጣሬ ይመራል። የመጀመርያው ጥያቄ ግን «እንዴት ነው ነገሮችን የምናስተካከለው» ወደሚለው ይመራል።
የዚህ አባባል ትርጉም ባጭሩ እንዲህ ነው፤ ችግርህን ሙሉበሙሉ የጠላቴ ጥፋት ነው ካልክ ለጠላት ያጋለጡህን የራስህን ድክመቶች አታምንም አታርምም። ጠላትን በቀጥታ በማጥፋት ላይ ብቻ ታተኩራለህ፤ ካቃተህ ተስፋ ትቆርጣለህ።
ምሳሌ፤ ህወሓት ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ተቃዋሚዎች መደራጀት ሳይችሉ፤ ገንዘብና አቅም መሰብሰብ ሳይችሉ፤ ምንም አይነት የተደራጀ የህዝብ ድጋፍ መሰብሰብ ሳይችሉ እነዚህ መሰረታዊ የህልውና ችግራቸውን ከማረም ይልቅ ያላቸውን ጊዜና አቅም ህወሓትን በመኮነን ብቻ አባከኑ። በዚህ ምክንያት ተቃዋሚዎቹ ህወሓትን ሊጎዱት አልቻልም። መጨረሻ ላይ ህወሓት የፈረሰው በራሱ ያጠመደው የጎሳ ብሄረተኝነት አደጋ ነው።
ዛሬም የኢትዮጵያዊነት የፖለቲካ ጎራ ተመሳሳይ ስህተት ላይ ይመስለኛል። ችግራችን ሁሉ የህወሓት ጥፋት ነው እያለ የራሱን ችግር እንኳን ለመፍታት ለማመንም ዝግጁ አይመስለኝም። ለምንድነው ህወሓት እንደዚህ ጠንክሮ የሚቀናቀነን? ለምንድነው መጀመሪያውኑ ህወሓት ሊገዛን የቻለው? ህወሓት ከየት ነው የመጣው? እነዚህ ጥያቄዎች ጥይቀን በትክክል ብንመልስ የራሳችንን ድክመቶች አይተን አርመን ህወሓትን በተሻለ ደረጃ መግጠም እንችላለን። ግን አላደረግነውም። በራሳችን ላይ ግምገማ አላደረግንም። ስህተቶቻችንን አላመንም። አላረምንም። በዚህ ምክንያት አላስፈላጊ ዋጋ እየከፈልን ነው።
መሆን የነበረበት እራሳችንን በዚህ መንገድ መገምገም ነበር፤ 1) ማርክሲስት ሆነን እርስ በርስ በመጣላታችንና ሀገሪቷን በማድከማችን እራሳችን ነን ህወሓትን የፈጠርነው ወይንም እንዲፈጠር ሜዳውን ያዘጋጀነው፤ 2) ሀውሓት ለረጅም ዓመታት የገዛን ምክንያት እኛ ቁጥራችን እጅግ አብላጫ ቢሆንም አብሮ መስራትና መደራጀት ስላቻልን ነው፤ 3) ዛሬም የህወሓትን ጦርነት በአጭሩ መጨረስ ያልቻልንበት ምክንያት አንድ ሆነን ተማምነን ተናበን መስራት ስላልቻልን ነው።
እራሳችንን በዚህ መንገድ ከገመገምን የችግሩ መፍትሄን አገኘን ማለት ነው። የፈረንጅ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ እንደ ማርክሲዝም አይነት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጎጂ እንደሆነ ተረድተን ከዛ አይነት አስተሳሰቦች እራሳችንን እናርቃለን። መተባበርና አንድ መሆን የግድ እንደሆነ ተረድተን ጥርጣሬ፤ መጠላለፍ፤ ምቀኝነት፤ ትእቢት ወዘተን አስወግደን በአንድነት እንሰራለን። እርስ በርስ ያሉንን ትናንሽ ልዩነቶች እንቅፋት እንዳይሆኑን ለትክክለኛው ጊዜ ና መድረክ ትተናቸው በአንድነት እንሰራለን። ለህወሓት ጥቃት ያጋለጡንን መሰረታዊ ችግሮቻችንን አርመን እንገኛለን። ይህንን ካደረግን ጠላትን በቀላሉ እናስወግዳለን።
No comments:
Post a Comment
ለሀሳብዎ አመሰግናለሁ!